መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።
ምዕራፍ 15
የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያም በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ።
2 ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።
3 ፤ ከእርሱ አስቀድሞ ባደረገው በአባቱ ኃጢአት ሁሉ ሄደ፤ ልቡም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አልነበረም።
4 ፤ ነገር ግን ልጁን ከእርሱ በኋላ ያስነሣ ዘንድ፥ ኢየሩሳሌምንም ያጸና ዘንድ አምላኩ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው፤
5 ፤ ዳዊት በዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አድርጎ ነበርና፥ ካዘዘውም ነገር ሁሉ ፈቀቅ አላለም ነበርና።
6 ፤ በኢዮርብዓምና በሮብዓም ልጅ በአብያም መካከል በዘመኑ ሁሉ ጠብ ነበረ።
7 ፤ የቀረውም የአብያም ነገር፥ ያደርገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በአብያምና በኢዮርብዓምም መካከል ሰልፍ ነበረ።
8 ፤ አብያምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት። ልጁም አሳ በፋንታው ነገሠ።
9 ፤ በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በሀያኛውም ዓመት አሳ በይሁዳ ላይ ነገሠ።
10 ፤ በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።
11 ፤ አሳ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
12 ፤ ከአገሩም ሰዶማውያንን አስወገደ፥ አባቶቹም ያደረጉትን ጣዖታትን ሁሉ አራቀ።
13 ፤ በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስለሠራች እናቱን መዓካን እቴጌ እንዳትሆን ሻራት፤ ጣዖትዋንም ሰበረው፥ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው።
14 ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ የአሳ ልብ ግን በዘመኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ነበረ።
15 ፤ አባቱ የቀደሰውንና እርሱም የቀደሰውን ወርቅና ብር ዕቃውንም ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባው።
16 ፤ በአሳና በእስራኤል ንጉሥ በባኦስ መካከል በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ።
17 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፤ ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ዘንድ ማንም እንዳይወጣ ወደ እርሱም ማንም እንዳይገባ አድርጎ ራማን ሠራ።
18 ፤ አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሥ ቤት መዛግብት የቀረውን ብርና ወርቅ ሁሉ ወስዶ በባሪያዎቹ እጅ ሰጣቸው፤ ንጉሡም አሳ በደማስቆ ለተቀመጠው ለአዚን ልጅ ለጠብሪሞን ልጅ ለሶርያ ንጉሥ ለወልደ አዴር።
19 ፤ በእኔና በአንተ መካከል በአባቴና በአባትህም መካከል ቃል ኪዳን ጸንቶአል፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ገጸ በረከት ሰድጄልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ ብሎ ሰደደ።
20 ፤ ወልደ አዴርም ለንጉሡ ለአሳ እሺ አለው፤ የሠራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰድዶ ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልቤት መዓካንና ኪኔሬትን ሁሉ የንፍታሌምንም አገር ሁሉ መታ።
21 ፤ ባኦስም ያን በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ትቶ በቴርሳ ተቀመጠ።
22 ፤ ንጉሡም አሳ በይሁዳ ሁሉ ላይ አዋጅ ነገረ፤ ማንም ነጻ አልነበረም፤ ባኦስም የሠራበትን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፥ ንጉሡም አሳ የብንያምን ጌባንና ምጽጳን ሠራበት።
23 ፤ የቀረውም የአሳ ነገር ሁሉ፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ያደረገውም ሁሉ፥ የሠራቸውም ከተሞች፥ በይሁዳ ነገሥት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ነገር ግን በሸመገለ ጊዜ እግሮቹ ታመሙ።
24 ፤ አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም ኢዮሣፍጥ በፋንታው ነገሠ።
25 ፤ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ።
26 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፥ በአባቱም መንገድ እስራኤልንም ባሳተበት ኃጢአት ሄደ።
27 ፤ ከይሳኮርም ቤት የሆነ የአኪያ ልጅ ባኦስ ተማማለበት፤ ናዳብና እስራኤልም ሁሉ ገባቶንን ከብበው ነበርና ባኦስ በፍልስጥኤም አገር ባለው በገባቶን ገደለው።
28 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሦስተኛው ዓመት ባኦስ ናዳብን ገደለው፥ በፋንታውም ነገሠ።
29 ፤
30 ፤ ንጉሥም በሆነ ጊዜ የኢዮርብዓምን ቤት ሁሉ መታ፤ ኢዮርብዓምም ስለ ሠራው ኃጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ስላስቈጣበት ማስቈጫ፥ በባሪያው በሴሎናዊው በአኪያ እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ እስኪያጠፋው ድረስ ከኢዮርብዓም አንድ ትንፋሽ ያለው አላስቀረም።
31 ፤ የቀረውም የናዳብ ነገርና ያደረገው ሁሉ፥ (
32 ፤) በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
33 ፤ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በእስራኤል ሁሉ ላይ በቴርሳ ንጉሥ ሆኖ ሀያ አራት ዓመት ነገሠ።
34 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፥ በኢዮርብዓምም መንገድ እስራኤልንም ባሳተበት ኃጢአት ሄደ።