መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22


ምዕራፍ 7

ሰሎሞንም የራሱን ቤት በአሥራ ሦስት ዓመት ሠራ፥ የቤቱንም ሥራ ሁሉ ጨረሰ።
2 ፤ የሊባኖስ ዱር ቤት የሚባል ቤትን ሠራ፤ ርዝመቱንም መቶ ክንድ፥ ስፋቱንም አምሳ ክንድ፥ ቁመቱንም ሠላሳ ክንድ አደረገ፤ የዝግባም እንጨት በሦስት ተራ በተሠሩ አዕማድ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአዕማዱም ላይ የዝግባ እንጨት አግዳሚ ሰረገሎች ነበሩ።
3 ፤ በአዕማዱም ላይ በነበሩ አግዳሚዎች ቤቱ በዝግባ ሳንቃ ተሸፍኖ ነበር፤ አዕማዱም በአንዱ ተራ አሥራ አምስት፥ በአንዱ ተራ አሥራ አምስት እየሆኑ አርባ አምስት ነበሩ።
4 ፤ መስኮቶቹም በሦስት ተራ ነበሩ፥ መስኮቶቹም ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር።
5 ፤ ደጆቹና መስኮቶቹም ሁሉ አራት ማዕዘን ነበሩ፤ መስኮቶቹም በሦስት ተራ ሆነው ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር።
6 ፤ አዕማዱም ያሉበቱን ቤት ሠራ፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ስፋቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ፤ በእርሱም ፊት ደግሞ አዕማድና መድረክ ያሉበት ወለል ነበረ።
7 ፤ ደግሞም የሚፈርድበት ዙፋን ያለበትን የፍርድ ቤት አደረገ። ከወለሉም አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ እንጨት ተሸፍኖ ነበር።
8 ፤ ከፍርድ ሰቀላ ወደ ውስጥ፥ በሌላውም አደባባይ ውስጥ የነበረውን መኖሪያ ቤት እንዲሁ ሠራ። እንደዚሁም ያለ ቤት ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ቤት ሠራ።
9 ፤ እነዚህም ሁሉ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ ጕልላቱ ድረስ በጥሩ በተጠረበና በውስጥና በውጭ በልክ በተከረከመ ድንጋይ ተሠርተው ነበር፤ በውጭውም እስከ ታላቁ አደባባይ ድረስ እንዲሁ ነበረ።
10 ፤ መሠረቱም አሥር ወይም ስምንት ክንድ በሆነ በጥሩና በታላቅ ድንጋይ ተሠርቶ ነበር።
11 ፤ በላዩም ልክ ሆኖ የተከረከመ ጥሩ ድንጋይና የዝግባ ሳንቃ ነበረ።
12 ፤ በታላቁም አደባባይ ዙሪያ የነበረው ቅጥር እንደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ውስጠኛው አደባባይ ቅጥርና እንደ ቤቱ ወለል ሦስቱ ተራ በተጠረበ ድንጋይ አንዱም ተራ በዝግባ ሳንቃ ተሠርቶ ነበር።
13 ፤ ንጉሡም ሰሎሞን ልኮ ኪራምን ከጢሮስ አስመጣ።
14 ፤ እርሱም ከንፍታሌም ወገን የነበረች የባል አልባ ሴት ልጅ ነበረ፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ናስ ሠራተኛ ነበረ፤ የናስንም ሥራ ሁሉ ይሠራ ዘንድ በጥበብና በማስተዋል በብልሃትም ተሞልቶ ነበር። ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን መጥቶ ሥራውን ሁሉ ሠራ።
15 ፤ ሁለቱን የናስ አዕማድ አደረገ፤ የአንዱም ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የዙሪያውም መጠን አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ የዓምዱም ውፍረት አንድ ጋት ነበረ፥ ውስጠ ክፍትም ነበረ። ሁለተኛውም ዓምድ እንዲሁ ነበረ።
16 ፤ በሁለቱም አዕማድ ራስ ላይ እንዲቀመጡ ከፈሰሰ ናስ ሁለት ጕልላት ሠራ፤ የአንዱም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ፥ የሁለተኛውም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ።
17 ፤ በአዕማዱም ራስ ላይ የነበሩትን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ሁለት እንደ መርበብ ሥራ አደረገ፤ አንዱም መርበብ ለአንዱ ጕልላት ሁለተኛውም መርበብ ለሁለተኛው ጕልላት ነበረ።
18 ፤ ሮማኖችንም ሠራ፤ በአንድ ጕልላት ዙሪያ በተራ ሁለት መቶ ሮማኖች ነበሩ፥ በአንድም መርበብ ላይ ሁለት ተራ ነበረ፤ እንዲሁም ለሁለተኛው ጕልላት አደረገ።
19 ፤ በወለሉም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ አራት ክንድ አድርጎ ቀረጸ።
20 ፤ በሁለቱም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ በመርበቡ ሥራ አጠገብ ሮማኖቹን አደረገ።
21 ፤ አዕማዱንም በመቅደሱ ወለል አጠገብ አቆማቸው፤ የቀኙንም ዓምድ አቁሞ ያቁም ብሎ ጠራው፤ የግራውንም ዓምድ አቁሞ በለዝ ብሎ ጠራው።
22 ፤ በአዕማዱም ራስ ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ ነበረ፤ እንዲሁም የአዕማዱ ሥራ ተጨረሰ።
23 ፤ ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር አሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ።
24 ፤ ከከንፈሩም በታች ለአንድ ክንድ አሥር ለአንድ ክንድም አሥር ጉብጉቦች አዞረበት፤ እርሱም በቀለጠ ጊዜ ጉብጉቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር።
25 ፤ ኵሬውም በአሥራ ሁለት በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱም ወደ ምዕራብ፥ ሦስቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር። ኵሬውም በላያቸው ነበረ፥ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ።
26 ፤ ውፍረቱም አንድ ጋት ነበረ፤ ከንፈሩም እንደ ጽዋ ከንፈር ተሠርቶ ነበር፤ እንደ ሱፍ አበባዎች ሆኖ ተከርክሞ ነበር። ሁለት ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ይይዝ ነበር።
27 ፤ አሥርም የናስ መቀመጫዎች ሠራ፤ የአንዱም መቀመጫ ርዝመት አራት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ ነበረ።
28 ፤ የመቀመጫውም ሥራ እንዲህ ነበረ፤ በክፈፎችም መካከል ያለው ሰንበር ይመስል ነበር።
29 ፤ በክፈፎቹም መካከል በነበሩ ሰንበሮች ላይ አንበሳዎችና በሬዎች ኪሩቤልም ነበሩ፤ እንዲሁም በክፈፎቹ ላይ ነበረ፤ ከአንበሳዎቹና ከበሬዎቹ በታች ሻኵራ የሚመስል ተንጠልጥሎ ነበር።
30 ፤ በየመቀመጫዎቹም ሁሉ አራት የናስ መንኰራኵሮች ነበሩባቸ፤ መንኰራኵሮቹም የሚዞሩበትን የናስ ወስከምት ሠራ፤ ከመታጠቢያውም ሰን በታች በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት በምስል የፈሰሱ እግሮች ነበሩ።
31 ፤ በክፈፉም ውስጥ የነበረ አንገት አንድ ክንድ ነበረ፤ አንገቱም ድቡልቡል ነበረ፥ ቁመቱም ክንድ ተኩል ነበረ። በአንገቱም ላይ ቅርጽ ነበረበት፤ ክፈፉ ግን አራት ማዕዘን ነበረ እንጂ ድቡልቡል አልነበረም።
32 ፤ አራቱም መንኰራኵሮች ከሰንበሮቹ በታች ነበሩ፤ የመንኰራኵሮቹም ወስከምት በመቀመጫው ውስጥ ነበረ፤ የመንኰራኵሩም ቁመት ክንድ ተኩል ነበረ።
33 ፤ የመንኰራኵሮቹም ሥራ እንደ ሰረገላ መንኰራኵር ነበረ፥ ወስከምቶቹና የመንኰራኵሮቹ ክፈፍ ቅትርቶቹም ወስከምቱም የሚገባበት ቧምቧ ሁሉ በምስል የፈሰሰ ነበር።
34 ፤ በእያንዳንዱም መቀመጫ በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት ደገፋዎች ነበሩ፤ ደገፋዎቹም ከመቀመጫው ጋር ተገጥመው ነበር።
35 ፤ በመቀመጫውም ላይ ስንዝር የሚሆን ድቡልቡል ነገር ነበረ፤ በመቀመጫውም ላይ የነበሩ መያዣዎችና ሰንበሮች ከእርሱ ጋር ይጋጠሙ ነበር።
36 ፤ በመያዣውና በሰንበሮቹ ላይ ኪሩቤልንና አንበሳዎችን የዘንባባውንም ዛፍ እንደ መጠናችው ቀረጸ፥ በዙሪያውም ሻኵራ አደረገ።
37 ፤ እንዲሁ አሥሩን መቀመጫዎች ሠራ፤ ሁሉም በምስልና በመጠን በንድፍም ትክክሎች ነበሩ።
38 ፤ አሥሩንም የናስ መታጠቢያ ሰን ሠራ፤ አንዱ መታጠቢያ ሰን አርባ የባዶስ መስፈሪያ ያነሣ ነበር፤ እያንዳንዱም መታጠቢያ ሰን አራት ክንድ ነበረ፤ በአሥሩም መቀመጫዎች ላይ በእያንዳንዱ አንድ አንድ መታጠቢያ ሰን ይቀመጥ ነበር።
39 ፤ አምስቱንም መቀመጫዎች በቤቱ ቀኝ፥ አምስቱንም በቤቱ ግራ አኖራቸው፤ ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው።
40 ፤ ኪራምም ምንችቶችንና መጫሪያዎችን ድስቶችንም ሠራ፤ ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ።
41 ፤ ሁለቱም አዕማድ፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ኩብ የሚመስሉትን ጕልላቶች፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች፥
42 ፤ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ለእያንዳንዱ መርበብ በሁለት በሁለት ተራ አድርጎ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ።
43 ፤ አሥሩንም መቀመጫዎች፥ በመቀመጫዎችም ላይ የሚቀመጡትን አሥሩን መታጠቢያ ሰን፥
44 ፤ አንዱንም ኵሬ፥ ከኵሬውም በታች የሚሆኑትን አሥራ ሁለቱን በሬዎች፥
45 ፤ ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም አደረገ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራው ይህ ዕቃ ሁሉ የጋለ ናስ ነበረ።
46 ፤ በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጸርታን መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው።
47 ፤ ሰሎሞንም ዕቃውን ሁሉ ሳያስመዝን አኖረ፤ የናሱም ሚዛን ከብዛቱ የተነሣ አይቈጠርም ነበር።
48 ፤ ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ አሠራ፤ የወርቁን መሠዊያ፥ የገጹም ኅብስት የነበረበትን የወርቅ ገበታ፥
49 ፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት አምስቱ በቀኝ አምስቱም በግራ የሚቀመጡትን ከጥሩ ወርቅ የተሠሩትንም መቅረዞች፥ የወርቁንም አበባዎችና ቀንዲሎች መኰስተሪያዎችም፥
50 ፤ ከጥሩ ወርቅም የተሠሩትን ጽዋዎችና ጕጠቶች፥ ድስቶቹንና ጭልፋዎቹንም፥ ማንደጃዎቹንም፥ ለውስጠኛውም ቤት ለቅድስተ ቅዱሳን ደጆች ለቤተ መቅደሱም ደጆች የሚሆኑትን የወርቅ ማጠፊያዎች አሠራ።
51 ፤ እንዲሁ ንጉሡ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሠራው ሥራ ሁሉ ተፈጸመ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን፥ ብርና ወርቅ ዕቃም፥ ሰሎሞን አገባ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ በነበሩ ግምጃ ቤቶች አኖረው።