መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22


ምዕራፍ 21

ለኢይዝራኤላዊውም ለናቡቴ በሰማርያ ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን ቦታ ነበረው።
2 ፤ አክዓብም ናቡቴን። በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ቦታ አደርገው ዘንድ የወይን ቦታህን ስጠኝ፤ ስለ እርሱም ከእርሱ የተሻለ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ወይም ብትወድድ ግምቱን ገንዘብ እሰጥሃለሁ ብሎ ተናገረው።
3 ፤ ናቡቴም አክዓብን። የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ አለው።
4 ፤ ኢይዝራኤላዊውም ናቡቴ። የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም ብሎ ስለ ተናገረው አክዓብ ተቈጥቶና ተናድዶ ወደ ቤቱ ገባ። በአልጋውም ላይ ተጋድሞ ፊቱን ተሸፋፈነ፥ እንጀራም አልበላም።
5 ፤ ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ መጥታ። ልብህ የሚያዝን እንጀራስ የማትበላ ስለምንድር ነው? አለችው።
6 ፤ እርሱም። ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን። የወይንህን ቦታ በገንዘብ ስጠኝ፤ ወይም ብትወድድ በፋንታው ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ ብዬ ተናገርሁት፤ እርሱ ግን። የወይን ቦታዬን አልሰጥህም ብሎ ስለ መለሰልኝ ነው አላት።
7 ፤ ሚስቱም ኤልዛቤል። አንተ አሁን የእስራኤልን መንግሥት ትገዛለህን? ተነሣ እንጀራም ብላ፥ ልብህም ደስ ይበላት፤ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ አለችው።
8 ፤ በአክዓብም ስም ደብዳቤ ጻፈች፥ በማኅተሙም አተመችው፤ በከተማው ወደ ነበሩትና ከናቡቴም ጋር ወደ ተቀመጡት ሽማግሌዎችና ከበርቴዎች ደብዳቤውን ላከች።
9 ፤ በደብዳቤውም። ስለ ጾም አዋጅ ንገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀምጡት፤
10 ፤ ሁለትም ምናምንቴ ሰዎች በፊቱ አስቀምጡና። እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው ይመስክሩበት፤ አውጥታችሁም እስኪሞት ድረስ ውገሩት ብላ ጻፈች።
11 ፤ በከተማውም የተቀመጡት የከተማው ሰዎችና ሽማግሌዎች ከበርቴዎችም ኤልዛቤል እንዳዘዘቻቸውና ወደ እነርሱ በተላከው ደብዳቤ እንደ ተጻፈ እንዲሁ አደረጉ።
12 ፤ የጾም አዋጅ ነገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀመጡት።
13 ፤ ሁለቱም ምናምንቴ ሰዎች ገብተው በፊቱ ተቀመጡ፤ ምናምንቴዎቹ ሰዎችም በሕዝቡ ፊት። ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው በናቡቴ ላይ መሰከሩ። የዚያን ጊዜም ከከተማ አውጥተው እስኪሞት ድረስ ወገሩት።
14 ፤ ወደ ኤልዛቤልም። ናቡቴ ተወግሮ ሞተ ብለው ላኩ።
15 ፤ ኤልዛቤልም ናቡቴ ተወግሮ እንደ ሞተ በሰማች ጊዜ ኤልዛቤል አክዓብን። ናቡቴ ሞቶአል እንጂ በሕይወት አይደለምና በገንዘብ ይሰጥህ ዘንድ እንቢ ያለውን የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ ተነሥተህ ውረስ አለችው።
16 ፤ አክዓብም ናቡቴ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ ይወርሰው ዘንድ ወደ ኢይዝራኤላዊው ወደ ናቡቴ ወይን ቦታ ሊወርድ ተነሣ።
17 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ።
18 ፤ ተነሥተህ በሰማርያ የሚኖረውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ እነሆ፥ ይወርሰው ዘንድ በወረደበት በናቡቴ የወይን ቦታ ውስጥ አለ።
19 ፤ አንተም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ገድለህ ወረስኸውን? ብለህ ንገረው። ደግሞም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል ብለህ ንገረው።
20 ፤ አክዓብም ኤልያስን። ጠላቴ ሆይ፥ አገኘኸኝን? አለው። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት። አግኝቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ለማድረግ ራስህን ሽጠሃልና።
21 ፤ እነሆ፥ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፥ ፈጽሞም እጠርግሃለሁ፥ ከአክዓብም በእስራኤል ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ አጠፋለሁ፤
22 ፤ በሥራህም አስቈጥተኸኛልና፥ እስራኤልንም አስተሃልና ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።
23 ፤ ደግሞ እግዚአብሔር ስለ ኤልዛቤል። በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ኤልዛቤልን ውሾች ይበሉአታል ብሎ ተናገረ።
24 ፤ ከአክዓብም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።
25 ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፋት ለመሥራት ራሱን እንደ ሸጠ፥ ሚስቱም ኤልዛቤል እንደ ነዳችው፥ እንደ አክዓብ ያለ ሰው አልነበረም።
26 ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ያጠፋቸው አሞራውያን እንደ ሠሩት ሁሉ፥ ጣዖታትን በመከተል እጅግ ርኩስ ነገር ሠራ።
27 ፤ አክዓብም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ ገላውን ማቅ አለበሰ፥ ጾመም፥ በማቅ ላይም ተኛ፥ ቅስስ ብሎም ሄደ።
28
29 ፤ ደግሞም። አክዓብ በፊቴ እንደ ተዋረደ አየህን? በፊቴ የተዋረደ ስለ ሆነ በልጁ ዘመን በቤቱ ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ እንጂ በእርሱ ዘመን ክፉ ነገር አላመጣም የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ መጣ።