መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22


ምዕራፍ 4

ንጉሡም ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር።
2 ፤ የነበሩትም አለቆች እነዚህ ናቸው፤ የሳዶቅ ልጅ ካህኑ ዓዛርያስ፥
3 ፤ ጸሐፊዎቹም የሴባ ልጆች ኤልያፍና አኪያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ፥
4 ፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፤
5 ፤ የናታንም ልጅ ዓዛርያስ የሹሞች አለቃ ነበረ፤ የናታንም ልጅ ዛቡድ የንጉሡ አማካሪና ወዳጅ ነበረ፤
6 ፤ አሒሳርም የቤት አዛዥ፥ የዓብዳም ልጅ አዶኒራም አስገባሪ ነበረ።
7 ፤ ለንጉሡና ለቤተ ሰቡም ቀለብ የሚሰጡ በእስራኤል ሁሉ ላይ አሥራ ሁለት ሹሞች ለሰሎሞን ነበሩት። ከዓመቱ ውስጥ አንዱን ወር እያንዳንዳቸው ይቀልቡ ነበር።
8 ፤ ስማቸውም ይህ ነበረ፤ በተራራማው አገር በኤፍሬም የሑር ልጅ፤
9 ፤ በማቃጽና በሸዓልቢም በቤትሳሚስና በኤሎንቤትሐናን የዴቀር ልጅ፤
10 ፤ በአሩቦት የሔሴድ ልጅ፥ ለእርሱም ሰኰትና የኦፌር አገር ሁሉ ነበረ፤
11 ፤ በዶር አገር ዳርቻ ሁሉ የአሚናዳብ ልጅ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ጣፈትን አግብቶ ነበር፤
12 ፤ ከቤትሳን ጀምሮ እስከ አቤልምሖላና እስከ ዮቅምዓም ማዶ ድረስ በታዕናክና በመጊዶ በጸርታንም አጠገብ በኢይዝራኤል በታች ባለው በቤትሳን ሁሉ የአሒሉድ ልጅ በዓና ነበረ፤
13 ፤ በሬማት ዘገለዓድ የጌበር ልጅ ነበረ፥ ለእርሱም በገለዓድ ያሉት የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች ነበሩ፤ ለእርሱም ደግሞ በባሳን በአርጎብ ዳርቻ ያሉት ቅጥርና የናስ መወረወሪያዎች የነበረባቸው ስድሳ ታላላቅ ከተሞች ነበሩበት፤
14 ፤ በመሃናይም የዒዶ ልጅ አሒናዳብ፤
15 ፤ በንፍታሌም አኪማአስ ነበረ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ባስማትን አግብቶ ነበር፤
16 ፤ በአሴርና በበዓሎት የኩሲ ልጅ በዓና፤
17 ፤ በይሳኮር የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ፤
18 ፤ በብንያም የኤላ ልጅ ሳሚ፤
19 ፤ በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎንና በባሳን ንጉሥ በዐግ አገር፥ በገለዓድ አገር፥ የኡሪ ልጅ ጌበር ነበረ፤ በዚያችም ምድር ላይ እርሱ ብቻውን ሹም ነበረ።
20 ፤ ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር።
21 ፤ ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ግብጽ ዳርቻ እስከ ፍልስጥኤም ድረስ በመንግሥታት ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር፤ ግብርም ያመጡለት ነበር፥ በዕድሜውም ሙሉ ለሰሎሞን ይገዙ ነበር።
22 ፤ ለሰሎሞንም ለቀን ለቀኑ ቀለብ የሚሆን ሠላሳ ኮር መልካም ዱቄትና ስድሳ ኮር መናኛ ድቄት፥
23 ፤ ከዋላና ከሚዳቋ ከበረሀ ፍየልና ከሰቡ ወፎች በቀር አሥር ፍሪዳዎች ሀያም የተሰማሩ በሬዎች አንድ መቶም በጎች ነበረ።
24 ፤ ከወንዙ ወዲህ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ከወንዙም ወዲህ ባለው አገር ሁሉ ላይ ከቲፍሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ ነግሦ ነበር፤ በዙሪያውም ባለው በሁሉ ወገን ሰላም ሆኖለት ነበር።
25 ፤ በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።
26 ፤ ለሰሎሞንም በአርባ ሺህ ጋጥ የሚገቡ የሰረገላ ፈረሶች አሥራ ሁለትም ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት።
27 ፤ እነዚያም ሹሞች እያንዳንዱ በየወሩ ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ማዕድ የሚቀርቡትን ሁሉ ይቀልቡ ነበር፤ ምንም አያጎድሉም ነበር።
28 ፤ እያንዳንዱም እንደ ደንቡ ለፈረሶቹና ለሰጋር በቅሎች ገብስና ጭድ ወደ ስፍራቸው ያመጡ ነበር።
29 ፤ እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው።
30 ፤ የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ።
31 ፤ ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ።
32 ፤ እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ።
33 ፤ ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር።
34 ፤ ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር።