መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22


ምዕራፍ 12

እስራኤል ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ።
2 ፤ እንዲህም ሆነ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን በሰማ ጊዜ፥ እርሱም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ኰብልሎ በግብጽ ተቀምጦ ነበርና፥ በግብጽም ሳለ ልከው ጠርተውት ነበርና
3 ፤ ኢዮርብዓምና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ መጥተው ለሮብዓም።
4 ፤ አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት።
5 ፤ እርሱም። ሂዱ፥ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ ተመለሱ አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።
6 ፤ ንጉሡም ሮብዓም። ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ።
7 ፤ እነርሱም። ለዚህ ሕዝብ አሁን ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል ብለው ተናገሩት።
8 ፤ እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ።
9 ፤ እርሱም። አባትህ የጫኑብንን ቀንበር አቃልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው።
10 ፤ ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች። አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፥ አንተ ግን አቃልልልን ለሚሉህ ሕዝብ። ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች።
11 ፤ አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት።
12 ፤ ንጉሡም። በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ።
13 ፤ ንጉሡም ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው።
14 ፤ እንደ ብላቴኖችም ምክር። አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ ብሎ ተናገራቸው።
15 ፤ እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአኪያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ነገር እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተመድቦ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።
16 ፤ እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ ለንጉሡ። በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ፥ ወደ ድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ፥ አሁን ቤትህን ተመልከት ብለው መለሱለት። እስራኤልም ወደ ድንኳኖቻቸው ሄዱ።
17 ፤ በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው።
18 ፤ ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶኒራምን ሰደደ፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ደበደቡት፥ ሞተም። ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሰረገላው ወጣ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ።
19 ፤ እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ሸፈተ።
20 ፤ እስራኤልም ሁሉ ኢዮርብዓም እንደ ተመለሰ በሰሙ ጊዜ ልከው ወደ ሸንጎአቸው ጠሩት፥ በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሡት። ከብቻው ከይሁዳ ነገድ በቀረ የዳዊትን ቤት የተከተለ አንድ ሰው አልነበረም።
21 ፤ ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ የእስራኤልንም ቤት ወግተው መንግሥቱን ወደ ሰሎሞን ልጅ ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳ ቤት ሁሉና ከብንያም ነገድ የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰልፈኞች ሰዎች ሰበሰበ።
22 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሳማያ።
23 ፤ ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓምና ለይሁዳ ለብንያምም ቤት ሁሉ ለቀረውም ሕዝብ ሁሉ።
24 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፥ የእስራኤልንም ልጆች ወንድሞቻችሁን አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ ብለህ ንገራቸው ሲል መጣ። የእግዚአብሔርንም ቃል ሰሙ፥ እንደ እግዚአብሔርም ቃል ተመልሰው ሄዱ።
25 ፤ ኢዮርብዓምም በተራራማው በኤፍሬም አገር ሴኬምን ሠርቶ በዚያ ተቀመጠ፤ ደግሞም ከዚያ ወጥቶ ጵኒኤልን ሠራ።
26 ፤ ኢዮርብዓምም በልቡ። አሁን መንግሥቱ ወደ ዳዊት ቤት ይመለሳል።
27 ፤ ይህ ሕዝብ በእግዚአብሔር ቤት መሥዋዕትን ያቀርብ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ቢወጣ፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ወደ ጌታቸው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ይመለሳል፥ እኔንም ይገድሉኛል አለ።
28 ፤ ንጉሡም ተማከረ፥ ሁለትም የወርቅ ጥጆች አድርጎ። እስራኤል ሆይ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ትወጡ ዘንድ ይበዛባችኋል፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህን አማልክቶችህን እይ አላቸው።
29 ፤ አንዱን በቤቴል፥ ሁለተኛውንም በዳን አኖረ።
30 ፤ ለአንዱ ጥጃ ይሰግድ ዘንድ ሕዝቡ እስከ ዳን ድረስ ይሄድ ነበርና ይህ ኃጢአት ሆነ።
31 ፤ በኮረብቶቹም ላይ መስገጃዎች ሠራ፥ ከሌዊ ልጆች ካይደሉ ከሕዝብ ሁሉ ካህናትን አደረገ።
32 ፤ በስምንተኛው ወር በአሥራ አምስተኛውም ቀን በይሁዳ እንደሚደረግ በዓል ያለ በዓል አደረገ፥ በመሠዊያውም ላይ ሠዋ፤ ለሠራቸውም ጥጆች ይሠዋ ዘንድ እንዲሁ በቤቴል አደረገ፤ ለኮረብታ መስገጃዎችም የመረጣቸውን ካህናት በቤቴል አኖራቸው።
33 ፤ በስምንተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን በልቡ ባሰበው ቀን በቤቴል በሠራው መሠዊያ ላይ ሠዋ፤ ለእስራኤልም ልጆች በዓል አደረገላቸው፤ በመሠዊያውም ሠዋ፥ ዕጣንም ዐጠነ።