መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22


ምዕራፍ 20

የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር ጭፍራውን ሁሉ ሰበሰበ፤ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ነገሥት ነበሩ፥ ፈረሶችና ሰረገሎችም ነበሩ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበበ፥ ወጋትም።
2 ፤ ወደ እስራኤልም ንጉሥ ወደ አክዓብ።
3 ፤ ወልደ አዴር እንዲህ ይላል። ብርህና ወርቅህ ለእኔ ነው፤ ሴቶችህና መልካካሞቹም ልጆችህ ለእኔ ናቸው ብሎ ወደ ከተማይቱ መልእክተኞችን ላከ።
4 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ እንዳልህ ነው፤ እኔ ለእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው አለ።
5 ፤ ደግሞም መልእክተኞች ተመልሰው። ወልደ አዴር እንዲህ ይላል። ቀድሞ ብርህንና ወርቅህን ሴቶችህንና ልጆችህንም ትሰጠኛለህ ብዬ ልኬብህ ነበር፤
6 ፤ ነገም በዚህ ጊዜ ባሪያዎቼን እልክብሃለሁ፥ ቤትህንም የባሪያዎችህንም ቤቶች ይበረብራሉ፤ ደስ የሚያሰኛቸውንም ሁሉ በእጃቸው አድርገው ይወስዳሉ አሉ።
7 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ። ተመልከቱ፥ ይህም ሰው ክፉ እንዲሻ እዩ፤ ስለ ሴቶቼ ስለ ልጆቼ ስለ ብሬና ወርቄም ላከብኝ፥ እንቢም አላልሁም አለ።
8 ፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ። አትስማው፥ እሺም አትበለው አሉት።
9 ፤ ለወልደ አዴርም መልእክተኞች። ለጌታዬ ለንጉሥ። ለእኔ ለባሪያህ በመጀመሪያ የላክህብኝ ሁሉ አደርጋለሁ፤ ይህን ግን አደርገው ዘንድ አይቻለኝም በሉት አላቸው። መልእክተኞችም ተመልሰው ይህን አወሩለት።
10 ፤ ወልደ አዴርም። ለሚከተለኝ ሕዝብ የሰማርያ ትቢያ ጭብጥ ጭብጥ ይበቃው እንደ ሆነ፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህን ይጨምሩብኝ ብሎ ላከበት።
11 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ። በቃ፤ ለሰልፍ የሚታጠቅ ጋሻ ጦሩን እንደሚያወልቅ አይመካ አለው።
12 ፤ ወልደ አዴርም ያን ነገር በሰማ ጊዜ ከነገሥታቱ ጋር በድንኳኑ ውስጥ ይጠጣ ነበር፤ ባሪያዎቹንም። ተሰለፉ አላቸው፤ እነርሱም በከተማይቱ ትይዪ ተሰለፉ።
13 ፤ እነሆም፥ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ ቀርቦ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ብዙ ጭፍራ ሁሉ ታያለህን? እነሆ፥ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ አለ።
14 ፤ አክዓብም። በማን? አለ፤ እርሱም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በአውራጆቹ አለቆች ጕልማሶች አለ፤ እርሱም። ሰልፉን ማን ይጀምራል? አለ፤ እርሱም። አንተ አለው።
15 ፤ የአውራጆቹንም አለቆች ጕልማሶች ቈጠረ፥ ሁለት መቶም ሠላሳ ሁለት ነበሩ፤ ከእነርሱም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ሁሉ፥ ቈጠረ፥ ሰባትም ሺህ ነበሩ።
16 ፤ ቀትርም በሆነ ጊዜ ወጡ፤ ወልደ አዴር ረዳቶቹም ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት እየጠጡ በድንኳን ውስጥ ይሰክሩ ነበር።
17 ፤ የአውራጆቹም አለቆች ጕልማሶች አስቀድመው ወጡ፤ ወልደ አዴርም መልእክተኞችን ላከ፥ እነርሱም። ሰዎች ከሰማርያ ወጥተዋል ብለው ነገሩት።
18 ፤ እርሱም። ለዕርቅ ወይም ለሰልፍ መጥተው እንደ ሆነ በሕይወታቸው ያዙአቸው አለ።
19 ፤ እነዚህም የአውራጆች አለቆች ጕልማሶች ከከተማይቱ ወጡ፥ ሠራዊትም ተከተላቸው።
20 ፤ ሁሉም በእያንዳንዱ በፊቱ የነበረውን ሰው ገደለ፥ ሶርያውያንም ሸሹ፤ እስራኤልም አሳደዱአቸው፥ የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር በፈረሱ አመለጠ።
21 ፤ የእስራኤል ንጉሥም ወጥቶ ፈረሶቹንና ሰረገሎቹን ያዘ፥ ሶርያውያንንም በታላቅ ውጊት ገደላቸው።
22 ፤ ነቢዩም ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ። የሶርያ ንጉሥ በሚመጣው ዓመት ይመጣብሃልና ሂድ፥ በርታ፥ የምታደርገውንም ተመልከትና እወቅ አለው።
23 ፤ የሶርያም ንጉሥ ባሪያዎች እንዲህ አሉት። አምላካቸው የተራሮች አምላክ ነው፤ ስለዚህ በርትተውብን ነበር፤ ነገር ግን በሜዳ ላይ ከእነርሱ ጋር ብንዋጋ በእርግጥ እንበረታባቸዋለን።
24 ፤ ይህንም አድርግ፤ ከጭፍሮችህ ነገሥታቱን አርቅ፥ በፋንታቸውም አለቆችን ሹም።
25 ፤ አንተም ቀድሞ እንደ ጠፋብህ ሠራዊት፥ ፈረሱን በፈረስ ፋንታ፥ ሰረገላውንም በሰረገላ ፋንታ፥ ሠራዊትን ቍጠር፤ በሜዳም ላይ ከእነርሱ ጋር እንዋጋለን፥ በእርግጥም እንበረታባቸዋለን። ምክራቸውንም ሰማ፥ እንዲሁም አደረገ። ፕ
26 ፤ በሚመጣውም ዓመት ወልደ አዴር ሶርያውያንን አሰለፈ፥ ከእስራኤልም ጋር ይዋጋ ዘንድ ወደ አፌቅ ወጣ።
27 ፤ የእስራኤልም ልጆች ተሰለፉ፥ ሊገጥሙአቸውም ወጡ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ሁለት ትናንሾች የፍየል መንጋዎች ሆነው በፊታቸው ሰፈሩ፤ ሶርያውያን ግን ምድሩን ሞልተው ነበር።
28 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ቀርቦ የእስራኤልን ንጉሥ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሶርያውያን። እግዚአብሔር የተራሮች አምላክ ነው እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ታላቅ ጭፍራ ሁሉ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ አለው።
29 ፤ እነዚህም በእነዚያ ትይዩ ሰባት ቀን ያህል ሰፈሩ፤ በሰባተኛውም ቀን ተጋጠሙ፥ የእስራኤልም ልጆች ከሶርያውያን በአንድ ቀን መቶ ሺህ እግረኛ ገደሉ።
30 ፤ የቀሩትም ወደ አፌቅ ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሸሹ፤ ቅጥሩም በቀሩት በሀያ ሰባት ሺህ ሰዎች ላይ ወደቀ። ወልደ አዴርም ሸሽቶ ወደ ከተማይቱ ወደ እልፍኙ ውስጥ ገባ።
31 ፤ ባሪያዎቹም። እነሆ፥ የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሐሪዎች እንደ ሆኑ ሰምተናል፤ በወገባችን ማቅ እንታጠቅ፥ በራሳችንም ገመድ እንጠምጥም፥ ወደ እስራኤልም ንጉሥ እንውጣ፤ ምናልባት ነፍስህን ይምራታል አሉት።
32 ፤ ወገባቸውንም በማቅ ታጠቁ፥ በራሳቸውም ገመድ ጠመጠሙ፥ ወደ እስራኤልም ንጉሥ መጥተው። ባሪያህ ወልደ አዴር። ነፍሴን ትምራት ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎአል አሉት። እርሱም። ገና በሕይወቱ አለን? ወንድሜ ነው አለ።
33 ፤ ሰዎቹም የደግ ምልክት አደረጉትና ቃሉን ከአፉ ተቀብለው። ወንድምህ ወልደ አዴር አለ አሉት። እርሱም። ሂዱ፥ አምጡት አለ። ወልደ አዴርም ወደ እርሱ ወጣ፥ በሰረገላውም ላይ አስቀመጠው።
34 ፤ ወልደ አዴርም። አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልስልሃለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገ አንተ በደማስቆ ገበያ ታደርጋለህ አለው። አክዓብም። እኔም በዚህ ቃል ኪዳን እሰድድሃለሁ አለ። ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳን አድርጎ ሰደደው።
35 ፤ ከነቢያትም ወገን አንድ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ባልንጀራውን። ምታኝ አለው። ሰውዮውም ይመታው ዘንድ እንቢ አለ።
36 ፤ እርሱም። የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና እነሆ፥ ከእኔ በራቅህ ጊዜ አንበሳ ይገድልሃል አለው። ከእርሱም በራቀ ጊዜ አንበሳ አግኝቶ ገደለው።
37 ፤ ደግሞም ሌላ ሰው አግኝቶ። ምታኝ አለው። ሰውዮውም መታው፥ በመምታቱም አቈሰለው።
38 ፤ ነቢዩም ሄዶ በመንገድ አጠገብ ንጉሡን ቆየው፤ ዓይኖቹንም በቀጸላው ሸፍኖ ተሸሸገ።
39 ፤ ንጉሡም ባለፈ ጊዜ ወደ እርሱ ጮኸ። ባሪያህ ወደ ሰልፍ መካከል ወጣ፤ እነሆም፥ አንድ ሰው ፈቀቅ ብሎ ወደ እኔ አንድ ሰው አመጣና። ይህን ሰው ጠብቅ፥ ቢኰበልልም ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ትሆናለች፥ ወይም አንድ መክሊት ብር ትከፍላለህ አለኝ።
40 ፤ ባሪያህም ወዲህና ወዲያ ሲመለከት ጠፋ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ። ፍርድህ እንዲሁ ይሆናል፤ አንተ ፈርድኸዋል አለው።
41 ፤ ፈጥኖም ቀጸላውን ከዓይኑ አነሣ የእስራኤልም ንጉሥ ከነቢያት ወገን እንደ ሆነ አወቀው።
42 ፤ እርሱም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ እርም ያልሁትን ሰው ከእጅህ አውጥተሃልና ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ሕዝብህም በሕዝቡ ፋንታ ይሆናሉ አለው።
43 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ እየተቈጣና እየተናደደ ወደ ቤቱ ተመለሰ፥ ወደ ሰማርያም መጣ።