መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።
ምዕራፍ 18
ከብዙ ቀንም በኋላ በሦስተኛው ዓመት። ሂድ፥ ለአክዓብ ተገለጥ፥ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ።
2 ፤ ኤልያስም ለአክዓብ ይገለጥ ዘንድ ሄደ፤ በሰማርያም ራብ ጸንቶ ነበር።
3 ፤ አክዓብም የቤቱን አዛዥ አብድዩን ጠራ፤ አብድዩ እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ነበር።
4 ፤ ኤልዛቤልም የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ እርሱ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውኃ ይመግባቸው ነበር።
5 ፤ አክዓብም አብድዩን። በአገሩ መካከል ወደ ውኃው ምንጭ ሁሉና ወደ ወንዝ ሁሉ ሂድ፤ እንስሶችም ሁሉ እንዳይጠፉ ፈረሶችንና በቅሎችን የምናድንበት ሣር ምናልባት እናገኛለን አለው።
6 ፤ ሁለቱም የሚመለሱበትን አገር ተካፈሉ፤ አክዓብም ለብቻው በአንድ መንገድ አብድዩም ለብቻው በሌላ መንገድ ሄዱ።
7 ፤ አብድዩም በመንገድ ሲሄድ፥ እነሆ፥ ኤልያስ ተገናኘው፤ አብድዩም አወቀው፥ በግምባሩም ተደፍቶ። ጌታዬ ሆይ፥ ኤልያስ አንተ ነህን? አለ።
8 ፤ ኤልያስም። እኔ ነኝ ሄደህ ለጌታህ። ኤልያስ ተገኝቶአል በል አለው።
9 ፤ አብድዩም አለ። እኔን ባሪያህን እንዲገድል በአክዓብ እጅ አሳልፈህ ትሰጠኝ ዘንድ ምን ኃጢአት አድርጌአለሁ?
10 ፤ አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! ጌታዬ ይፈልግህ ዘንድ ያልላከበት ሕዝብ ወይም መንግሥት የለም፤ ሁሉም። በዚህ የለም ባሉ ጊዜ አንተን እንዳላገኙ መንግሥቱንና ሕዝቡን አምሎአቸው ነበር።
11 ፤ አሁንም፥ እነሆ። ሂድ፥ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር ትለኛለህ።
12 ፤ እኔም ከአንተ ጥቂት ራቅ ስል የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደማላውቀው ስፍራ ይወስድሃል፤ እኔም ገብቼ ለአክዓብ ስናገር፥ ባያገኝህ ይገድለኛል፤ እኔም ባሪያህ ከትንሽነቴ ጀምሬ እግዚአብሔርን እፈራ ነበር።
13 ፤ ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ፥ መቶውን የእግዚአብሔር ነቢያት ወስጄ፥ አምሳ አምሳውንም በዋሻ ውስጥ ሸሽጌ፥ እንጀራና ውኃ የመገብኋቸው፥ ይህ ያደርግሁት ነገር በውኑ ለጌታዬ አልታወቀህምን?
14 ፤ አሁንም። ሄደህ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር ትላለህ፤ እርሱም ይገድለኛል።
15 ፤ ኤልያስም። በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ ዛሬ ለእርሱ እገለጣለሁ አለ።
16 ፤ አብድዩም አክዓብን ሊገናኘው ሄደ፥ ነገረውም፤ አክዓብም ኤልያስን ሊገናኘው መጣ።
17 ፤ አክዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ። እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን? አለው።
18 ፤ ኤልያስም። እስራኤልን የምትገለባብጡ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም።
19 ፤ አሁንም ልከህ እስራኤልን ሁሉ፥ በኤልዛቤልም ማዕድ የሚበሉትን አራት መቶ አምሳ የበኣልን ነቢያት፥ አራት መቶም የማምለኪያ ዐፀድን ነቢያት ወደ እኔ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብ አለ።
20 ፤ አክዓብም ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ ልኮ ነቢያቱን ሁሉ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ።
21 ፤ ኤልያስም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ። እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ አለ። ሕዝቡም አንዲት ቃል አልመለሱለትም።
22 ፤ ኤልያስም ሕዝቡን አለ። ከእግዚአብሔር ነቢያት እኔ ብቻ ቀርቻለሁ፤ የበኣል ነቢያት ግን አራት መቶ አምሳ ሰዎች ናቸው።
23 ፤ ሁለት ወይፈኖች ይሰጡን፤ እነርሱም አንድ ወይፈን ይምረጡ፥ እየብልቱም ይቍረጡት፥ በእንጨትም ላይ ያኑሩት፥ በበታቹም እሳት አይጨምሩ፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረዋለሁ፥ በበታቹም እሳት አልጨምርም።
24 ፤ እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፥ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፥ እርሱ አምላክ ይሁን። ሕዝቡም ሁሉ። ይህ ነገር መልካም ነው ብለው መለሱ።
25 ፤ ኤልያስም የበኣልን ነቢያት። እናንተ ብዙዎች ናችሁና አስቀድማችሁ አንድ ወይፈን ምረጡና አዘጋጁ፤ የአምላካችሁንም ስም ጥሩ፥ በበታችሁም እሳት አትጨምሩ አላቸው።
26 ፤ ወይፈኑንም ወስደው አዘጋጁ፥ ከጠዋትም እስከ ቀትር ድረስ። በኣል ሆይ፥ ስማን እያሉ የበኣልን ስም ጠሩ። ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስም አልነበረም፤ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ያሸበሽቡ ነበር።
27 ፤ በቀትርም ጊዜ ኤልያስ። አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፤ ምናልባት አሳብ ይዞታል፥ ወይም ፈቀቅ ብሎአል፥ ወይም ወደ መንገድ ሄዶአል፥ ወይም ተኝቶ እንደ ሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል እያለ አላገጠባቸው።
28 ፤ በታላቅም ቃል ይጮኹ፥ እንደ ልማዳቸውም ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ገላቸውን በካራና በቀጭኔ ይብዋጭሩ ነበር።
29 ፤ ቀትርም ካለፈ በኋላ መሥዋዕተ ሠርክ እስኪደርስ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስና የሚያደምጥም አልነበረም።
30 ፤ ኤልያስም ሕዝቡን ሁሉ። ወደ እኔ ቅረቡ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ። ፈርሶ የነበረውንም የእግዚአብሔርን መሠዊያ አበጀ።
31 ፤ ኤልያስም። ስምህ እስራኤል ይሆናል የሚል የእግዚአብሔር ቃል እንደ ደረሰለት እንደ ያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወሰደ።
32 ፤ ከድንጋዮችም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚያዝ ጕድጓድ ቈፈረ።
33 ፤ እንጨቱንም በተርታ አደረገ፥ ወይፈኑንም በብልት በብልቱ ቈረጠ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረና።
34 ፤ አራት ጋን ውኃ ሙሉ በሚቃጠለው መሥዋዕትና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ አሉ። ደግሞም። ድገሙ አለ፤ እነርሱም ደገሙ። እርሱም። ሦስተኛ አድርጉ አለ፤ ሦስተኛም አደረጉ።
35 ፤ ውኃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ደግሞም ጕድጓዱን በውኃ ሞላው።
36 ፤ መሥዋዕተ ሠርክ በሚቀርብበት ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቀርቦ። አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ።
37 ፤ አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፥ አቤቱ፥ ስማኝ አለ።
38 ፤ የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፥ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች።
39 ፤ ሕዝቡም ሁሉ ያንን ባዩ ጊዜ በግምባራቸው ተደፍተው። እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው አሉ።
40 ፤ ኤልያስም። ከበኣል ነቢያት አንድ ሰው እንዳያመልጥ ያዙ አላቸው። ያዙአቸውም፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ ወስዶ በዚያ አሳረዳቸው።
41 ፤ ኤልያስም አክዓብን። የዝናቡ ውሽንፍር እጅግ ነውና ተነሥተህ ውጣ፥ ብላም ጠጣም አለው።
42 ፤ አክዓብም ሊበላና ሊጠጣ ወጣ፤ ኤልያስም ወደ ቀርሜሎስ አናት ወጣ፤ ፊቱንም በጕልበቱ መካከል አድርጎ በግምባሩ ተደፋ።
43 ፤ ብላቴናውንም። ወጥተህ ወደ ባሕሩ ተመልከት አለው። ወጥቶም ተመልክቶም። ምንም የለም አለ። እርሱም። ሰባት ጊዜ ተመላለስ አለው። ብላቴናውም ሰባት ጊዜ ተመላለሰ።
44 ፤ በሰባተኛውም ጊዜ። እነሆ፥ የሰው እጅ የምታህል ታናሽ ደመና ከባሕር ወጥች አለ። እርሱም። ወጥተህ አክዓብን። ዝናብ እንዳይከለክልህ ሰረገላን ጭነህ ውረድ በለው አለ።
45 ፤ ከጥቂትም ጊዜ በኋላ ሰማዩ ከደመናውና ከነፋሱ የተነሣ ጨለመ፥ ብዙም ዝናብ ሆነ፤ አክዓብም በሰረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ።
46 ፤ የእግዚአብሔርም እጅ በኤልያስ ላይ ነበረች፤ ወገቡንም አሸንፍጦ ወደ ኢይዝራኤል እስኪገባ ድረስ በአክዓብ ፊት ይሮጥ ነበር።