ምዕራፍ 1

አክዓብም ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ።
2 ፤ አካዝያስም በሰማርያ በሰገነቱ ላይ ሳለ ከዓይነ ርግቡ ወድቆ ታመመ፤ እርሱም። ሂዱ ከዚህም ደዌ እድን እንደ ሆነ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ጠይቁ ብሎ መልእክተኞችን ላከ።
3 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ቴስብያዊውን ኤልያስን። ተነሣ፥ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቁ ዘንድ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን?
4 ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በላቸው አለው። ኤልያስም ሄደ።
5 ፤ መልእክተኞችም ወደ አካዝያስ ተመለሱ፥ እርሱም። ለምን ተመለሳችሁ? አላቸው።
6 ፤ እነርሱም። አንድ ሰው ሊገናኘን መጣና። ሂዱ፥ ወደ ላካችሁም ንጉሥ ተመልሳችሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ የላከህ በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በሉት አለን አሉት።
7 ፤ እርሱም። ሊገናኛችሁ የወጣው፥ ይህንስ ቃል የነገራችሁ ሰው መልኩ ምን ይመስላል? አላቸው።
8 ፤ እነርሱም። ሰውዮው ጠጕራም ነው፥ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር አሉት። እርሱም። ቴስብያዊው ኤልያስ ነው አለ።
9 ፤ ንጉሡም የአምሳ አለቃውን ከአምሳ ሰዎች ጋር ሰደደ፥ ወደ እርሱም ወጣ፤ እነሆም፥ በተራራ ራስ ላይ ተቀምጦ ነበር። እርሱም። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ንጉሡ። ውረድ ይልሃል አለው።
10 ፤ ኤልያስም መልሶ የአምሳ አለቃውን። እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፥ አንተንም፥ አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ አለው። እሳትም ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎቹን በላች።
11 ፤ ደግሞም ሌላ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ላከበት፤ እርሱም። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ንጉሡ። ፈጥነህ ውረድ ይላል ብሎ ተናገረ።
12 ፤ ኤልያስም። እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፥ አንተንም አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ አለው። የእግዚአብሔርም እሳት ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎቹን በላች።
13 ፤ ደግሞም ሦስተኛ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ሰደደ፤ ሦስተኛውም የአምሳ አለቃ ወጥቶ በኤልያስ ፊት በጕልበቱ ተንበረከከና። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ነፍሴና የእነዚህ የአምሳው ባሪያዎችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን።
14 ፤ እነሆ፥ እሳት ከሰማይ ወርዳ የፊተኞቹን ሁለቱን የአምሳ አለቆችና አምሳ አምሳውን ሰዎቻቸውን በላች፤ አሁን ግን ነፍሴ በፊትህ የከበረች ትሁን ብሎ ለመነው።
15 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን። ከእርሱ ጋር ውረድ፥ አትፍራውም አለው። ተነሥቶም ከእርሱ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ።
16 ፤ ኤልያስም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ መልእክተኞችን ልከሃልና ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም አለው።
17 ፤ ኤልያስም እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሞተ። ልጅም አልነበረውምና በይሁዳ ንጉሥ በኢዮሣፍጥ ልጅ በኢዮራም በሁለተኛው ዓመት ወንድሙ ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
18 ፤ አካዝያስ ያደረገው የቀረው ነገር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?