መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25


ምዕራፍ 15

በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በሀያ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ ነገሠ።
2 ፤ መንገሥም በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
3 ፤ አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
4 ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።
5 ፤ እግዚአብሔርም ንጉሡን ቀሠፈው፥ እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጻም ሆነ፥ በተለየ ቤትም ይቀመጥ ነበር፥ የንጉሡም ልጅ ኢዮአታም በንጉሥ ቤት ላይ ሠልጥኖ ለአገሩ ሕዝብ ይፈርድ ነበር።
6 ፤ የቀረውም የዓዛርያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
7 ፤ ዓዛርያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
8 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ስድስት ወር ነገሠ።
9 ፤ አባቶቹም እንዳደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳታቸው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም።
10 ፤ የኢያቤስም ልጅ ሰሎም ተማማለበት፥ በይብልዓም መትቶ ገደለው፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ።
11 ፤ የቀረውም የዘካርያ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
12 ፤ ለኢዩ። ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ ተብሎ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነበረ፤ እንዲሁም ሆነ።
13 ፤ በይሁዳ ንጉሠ በዖዝያን በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም ነገሠ፤ በሰማርያም አንድ ወር ያህል ነገሠ።
14 ፤ የጋዲም ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ መጣ፥ በሰማርያም የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን መታ፥ ገደለውም፤ በእርሱም ፋንታ ነገሠ።
15 ፤ የቀረውም የሰሎም ነገር፥ የተማማለውም ዓመፅ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
16 ፤ በዚያን ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ቲፍሳን በእርስዋም ያሉትን ሁሉ ዳርቻዋንም መታ፤ ይከፍቱለትም ዘንድ አልወደዱምና መታት፤ በእርስዋም የነበሩትን እርጉዞች ሁሉ ቀደዳቸው።
17 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ መንገሥ ጀመረ፤ በሰማርያም አሥር ዓመት ነገሠ።
18 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም።
19 ፤ በዘመኑም የአሦር ንጉሥ ፎሐ በምድሪቱ ላይ ወጣ፤ ምናሔምም መንግሥቱን በእጁ ያጸናለት ዘንድ የፎሐ እጅ ከእርሱ ጋር እንዲሆን አንድ ሺህ መክሊት ብር ሰጠው።
20 ፤ ምናሔምም ብሩን ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ በእስራኤል ባለ ጠጎች ሁሉ ላይ በእያንዳንዱ ላይ አምሳ ሰቅል ብር አስገብሮ አወጣ። የአሦርም ንጉሥ ተመለሰ፥ በአገሪቱም አልተቀመጠም።
21 ፤ የቀረውም የምናሔም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
22 ፤ ምናሔም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ፋቂስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
23 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ።
24 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም።
25 ፤ የሠራዊቱም አለቃ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ተማማለበት፥ በሰማርያም በንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ከአርጎብና ከአርያ ጋር መታው፤ ከእርሱም ጋር አምሳ የገለዓድ ሰዎች ነበሩ፤ ገደለውም፥ ፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ።
26 ፤ የቀረውም የፋቂስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
27 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሀያ ዓመትም ነገሠ።
28 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም።
29 ፤ በእስራኤልም ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮንና አቤልቤትመዓካን፥ ያኖዋንም፥ ቃዴስንና አሶርንም፥ ገለዓድንና ገሊላንም፥ የንፍታሌምን አገር ሁሉ ወሰደ፤ ወደ አሦርም አፈለሳቸው።
30 ፤ በዖዝያንም ልጅ በኢዮአታም በሀያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ ተማማለ፥ መትቶም ገደለው፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ።
31 ፤ የቀረውም የፋቁሔ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።
32 ፤ በእስራኤል ንጉሥ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ።
33 ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ የሳዶቅ ልጅ ኢየሩሳ ነበረች።
34 ፤ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ አባቱ ዖዝያን እንዳደረገ ሁሉ እንዲሁ አደረገ።
35 ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። እርሱም የላይኛውን የእግዚአብሔርን ቤት በር ሠራ።
36 ፤ የቀረውም የኢዮአታም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
37 ፤ በዚያም ወራት እግዚአብሔር የሶርያን ንጉሥ ረአሶንንና የሮሜልዩን ልጅ ፋቁሔን በይሁዳ ላይ መስደድ ጀመረ።
38 ፤ ኢዮአታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም አካዝ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።