መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25


ምዕራፍ 14

በእስራኤል ንጉሥ በኢዮአካዝ ልጅ በዮአስ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ።
2 ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
3 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ኢዮአስ እንዳደረገ ሁሉ እንጂ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም።
4 ፤ ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።
5 ፤ መንግሥቱም በጸናለት ጊዜ አባቱን የገደሉትን ባሪያዎች ገደለ።
6 ፤ በሙሴ ሕግ መጽሐፍም እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔርም። ሁሉ በኃጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆች አይሙቱ፥ ልጆችም በአባቶች አይሙቱ ብሎ እንዳዘዘ የነፍሰ ገዳዮቹን ልጆች አልገደለም።
7 ፤ እርሱም በጨው ሸለቆ ከኤዶምያስ አሥር ሺህ ሰው ገደለ፤ ሴላን በሰልፍ ወስዶ ስምዋን እስከ ዛሬ ድረስ ዮቅትኤል ብሎ ጠራት።
8 ፤ በዚያን ጊዜም አሜስያስ። ና እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞችን ላከ።
9 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ። የሊባኖስ ኵርንችት፥ ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው ብሎ ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኵርንችቱን ረገጠ።
10 ፤ ኤዶምያስን በእውነት መታህ፥ ልብህንም ከፍ ከፍ አደረግህ፤ በዚያ ተመካ፥ በቤትህም ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር ትወድቅ ዘንድ ስለ ምን መከራ ትሻለህ? ብሎ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ላከ።
11 ፤ አሜስያስ ግን አልሰማም፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወጣ፥ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤት ሳሚስ እርስ በርሳቸው ተያዩ።
12 ፤ ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ።
13 ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስክ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ።
14 ፤ ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ በመያዣም የተያዙትን ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
15 ፤ የቀረውም ያደረገው የዮአስ ነገር፥ ጭከናውም፥ ከይሁዳም ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንደ ተዋጋ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
16 ፤ ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮርብዓም በፋንታው ነገሠ።
17 ፤ የይሁዳም ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከዮአስ ሞት በኋላ አሥራ አምስት ዓመት ኖረ።
18 ፤ የቀረውም የአሜስያስ ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
19 ፤ በኢየሩሳሌምም የዓመፅ መሐላ አደረጉበት፥ እርሱም ወደ ለኪሶ ኰበለለ፤ በኋላውም ወደ ለኪሶ ላኩ፥ በዚያም ገደሉት።
20 ፤ በፈረስም ጭነው አመጡት፥ በኢየሩሳሌምም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ።
21 ፤ የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ የነበረውን ዓዛርያስን ወስዶ በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሠው።
22 ፤ ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ፥ ኤላትን ሠርቶ ወደ ይሁዳ መለሳት።
23 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ልጅ በአሜስያስ በአሥራ አምስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ አርባ አንድ ዓመትም ነገሠ።
24 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልንም ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት ሁሉ አልራቀም።
25 ፤ የጋትሔፌር በነበረው በአማቴ ልጅ በባሪያው በነቢዩ በዮናስ እጅ እንደ ተናገረው እንደ እስራኤል አምላክ እንደ እግዚአብሔር ቃል የእስራኤልን ድንበር ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ መለሰ።
26 ፤ የታሰረውና የተለቀቀውም እንደ ጠፋ፥ እስራኤልንም የሚረዳ እንዳልነበረ እግዚአብሔር እጅግ የመረረውን የእስራኤልን ጭንቀት አየ።
27 ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ስም ከሰማይ በታች ይደመስስ ዘንድ አልተናገረም፤ ነገር ግን በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም እጅ አዳናቸው።
28 ፤ የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ እንደ ተዋጋም፥ የይሁዳ የነበረውን ደማስቆንና ሐማትን ለእስራኤል እንደ መለሰ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
29 ፤ ኢዮርብዓምም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዘካርያ በፋንታው ነገሠ።