መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ።
ምዕራፍ 4
ከነቢያትም ወገን ሚስቶች አንዲት ሴት። ባሌ ባሪያህ ሞቶአል፤ ባሪያህም እግዚአብሔርን ይፈራ እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ፤ ባለ ዕዳ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል ብላ ወደ ኤልሳዕ ጮኸች።
2 ፤ ኤልሳዕም። አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ? በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ አላት። እርስዋም። ለእኔ ለባሪያህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም አለች።
3 ፤ እርሱም። ሄደሽ ከጐረቤቶችሽ ሁሉ ከሜዳ ባዶ ማድጋዎችን ተዋሺ፤ አታሳንሻቸውም አላት።
4 ፤ ገብተሽም ከአንቺና ከልጆችሽ በኋላ በሩን ዝጊ፥ ወደ እነዚህም ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን ገልብጪ፤ የሞላውንም ፈቀቅ አድርጊ አለ።
5 ፤ እንዲሁም ከእርሱ ሄዳ በሩን ከእርስዋና ከልጆችዋ በኋላ ዘጋች፤ እነርሱም ማድጋዎቹን ወደ እርስዋ ያመጡ ነበር፥ እርስዋም ትገለብጥ ነበር።
6 ፤ ማድጋዎቹም በሞሉ ጊዜ ልጅዋን። ደግሞም ማድጋ አምጣልኝ አለችው፤ እርሱም። ሌላ ማድጋ የለም አላት፤ ዘይቱም ቆመ።
7 ፤ መጥታም ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው፤ እርሱም። ሄደሽ ዘይቱን ሽጪ ለባለ ዕዳውም ክፈዪ፤ አንቺና ልጆችሽም ከተረፈው ተመገቡ አለ።
8 ፤ አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ ኤልሳዕ ወደ ሱነም አለፈ፥ በዚያም ታላቅ ሴት ነበረች፤ እንጀራ ይበላ ዘንድ የግድ አለችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር እንጀራ ሊበላ ወደዚያ ይገባ ነበር።
9 ፤ ለባልዋም። ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆነ አውቃለሁ።
10 ፤ ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋ ጠረጴዛ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደ እኛም ሲመጣ ወደዚያ ይገባል አለችው።
11 ፤ አንድ ቀንም ወደዚያ በመጣ ጊዜ ወደ ቤቱ ገብቶ በዚያ ዐረፈ።
12 ፤ ሎሌውንም ግያዝን። ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው።
13 ፤ በጠራትም ጊዜ በፊቱ ቆመች። እርሱም። እነሆ፥ ይህን ሁሉ አሳብ አሰብሽልኝ፤ አሁንስ ምን ላድርግልሽ? ለንጉሥ ወይስ ለሠራዊት አለቃ ልንገርልሽን? በላት አለው፤ እርስዋም። እኔ በወገኔ መካከል ተቀምጫለሁ ብላ መለሰች።
14 ፤ እርሱም። እንግዲህ ምን እናድርግላት? አለ። ግያዝም። ልጅ የላትም፤ ባልዋም ሸምግሎአል ብሎ መለሰ።
15 ፤ እርሱም። ጥራት አለ። በጠራትም ጊዜ በደጃፉ ቆመች።
16 ፤ እርሱም። በሚመጣው ዓመት በዚህ ወራት ወንድ ልጅ ትታቀፊአለሽ አለ፤ እርስዋም። አይደለም ጌታዬ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ባሪያህን እንዳትዋሻት እለምንሃለሁ አለች።
17 ፤ ሴቲቱም ፀነሰች፥ በዚያም ወራት በአዲሱ ዓመት ኤልሳዕ እንዳላት ወንድ ልጅ ወለደች።
18 ፤ ሕፃኑም አደገ፥ አንድ ቀንም እህል አጫጆች ወዳሉበት ወደ አባቱ ወጣ።
19 ፤ አባቱንም። ራሴን ራሴን አለው፤ እርሱም ሎሌውን። ተሸክመህ ወደ እናቱ ውሰደው አለው።
20 ፤ አንሥቶም ወደ እናቱ ወሰደው፤ በጕልበትዋም ላይ እስከ ቀትር ድረስ ተቀመጠ፥ ሞተም።
21 ፤ ወጥታም በእግዚአብሔር ሰው አልጋ ላይ አጋደመችው፥ በሩንም ዘግታበት ወጣች።
22 ፤ ባልዋንም ጠርታ። ወደ እግዚአብሔር ሰው በፍጥነት ደርሼ እመለስ ዘንድ አንድ ሎሌና አንድ አህያ ላክልኝ አለችው።
23 ፤ እርሱም። መባቻ ወይም ሰንበት ያይደለ ዛሬ ለምን ትሄጂበታለሽ? አለ። እርስዋም። ደኅና ነው አለች።
24 ፤ አህያውንም አስጭና ሎሌዋን። ንዳ፥ ሂድ፤ እኔ ሳላዝዝህ አታዘግየኝ አለችው።
25 ፤ እንዲሁም ሄደች፥ ወደ እግዚአብሔርም ሰው ወደ ቀርሜሎስ ተራራ መጣች። የእግዚአብሔርም ሰው ከሩቅ ባያት ጊዜ ሎሌውን ግያዝን፥ እነኋት ሱነማዊቲቱ መጣች፤
26 ፤ ትቀበላትም ዘንድ ሩጥና። በደኅናሽ ነውን? ባልሽ ደኅና ነውን? ልጅሽስ ደኅና ነውን? በላት አለው። እርስዋም። ደኅና ነው አለች።
27 ፤ ወደ ተራራው ወደ እግዚአብሔር ሰው በመጣች ጊዜ እግሮቹን ጨበጠች፤ ግያዝም ሊያርቃት ቀረበ፤ የእግዚአብሔርም ሰው። ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት፤ እግዚአብሔርም ያንን ከእኔ ሰውሮታል አልነገረኝምም አለ።
28 ፤ እርስዋም። በውኑ ከጌታዬ ልጅን ለመንሁን? እኔም አታታልለኝ አላልሁህምን? አለች።
29 ፤ ግያዝንም። ወገብህን ታጠቅ፥ በትሬንም በእጅህ ይዘህ ሂድ፤ ሰውም ብታገኝ ሰላም አትበል፥ እርሱም ሰላም ቢልህ አትመልስለት፤ በትሬንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኑር አለው።
30 ፤ የሕፃኑም እናት። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! አልተውህም አለች፤ ተነሥቶም ተከተላት።
31 ፤ ግያዝም ቀደማቸው፥ በትሩንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኖረው፤ ነገር ግን ድምፅ ወይም መስማት አልነበረም፤ እርሱንም ሊገናኘው ተመልሶ። ሕፃኑ አልነቃም ብሎ ነገረው።
32 ፤ ኤልሳዕም ወደ ቤት በገባ ጊዜ እነሆ፥ ሕፃኑ ሞቶ በአልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር።
33 ፤ ገብቶም በሩን ከሁለቱ በኋላ ዘጋ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ።
34 ፤ መጥቶም በሕፃኑ ላይ ተኛ፤ አፉንም በአፉ፥ ዓይኑንም በዓይኑ፥ እጁንም በእጁ ላይ አድርጎ ተጋደመበት፤ የሕፃኑም ገላ ሞቀ።
35 ፤ ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ፤ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕፃኑ ላይ ተጋደመ፤ ሕፃኑም ዓይኖቹን ከፈተ።
36 ፤ ግያዝንም ጠርቶ። ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው። ጠራትም፥ ወደ እርሱም በገባች ጊዜ። ልጅሽን አንሥተሽ ውሰጂ አላት።
37 ፤ ገብታም በእግሩ አጠገብ ወደቀች በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጅዋንም አንሥታ ወጣች።
38 ፤ ኤልሳዕም ዳግመኛ ወደ ጌልገላ መጣ፥ በምድርም ላይ ራብ ነበረ፤ የነቢያትም ልጆች በፊቱ ተቀምጠው ነበር፥ ሎሌውንም። ታላቁን ምንቸት ጣድ፥ ለነቢያት ልጆችም ወጥ ሥራ አለው።
39 ፤ አንዱም ቅጠላቅጠል ያመጣ ዘንድ ወደ ሜዳ ወጣ፥ የምድረበዳውንም ሐረግ አገኘ ከዚያም የበረሀ ቅል ሰበሰበ፥ ልብሱንም ሞልቶ ተመለሰ፥ መትሮም በወጡ ምንቸት ውስጥ ጨመረው፤ ምን እንደ ሆነ ግን አላወቁም።
40 ፤ ሰዎቹም ይበሉ ዘንድ ቀዱ፤ ወጡንም በቀመሱ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ በምንቸቱ ውስጥ ሞት አለ ብለው ጮኹ፤ ይበሉም ዘንድ አልቻሉም።
41 ፤ እርሱም። ዱቄት አምጡልኝ አለ፤ በምንቸቱም ውስጥ ጥሎ። ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ቅዱ አለ። በምንቸቱም ውስጥ ክፉ ነገር አልተገኘም።
42 ፤ አንድ ሰውም ከበኣልሻሊሻ የበኵራቱን እንጀራ፥ ሀያ የገብስ እንጀራ፥ የእህልም እሸት በአቁማዳ ይዞ ወደ እግዚአብሔር ሰው መጣ፤ እርሱም። ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው አለ።
43 ፤ ሎሌውም። ይህን እንዴት አድርጌ ለመቶ ሰው እሰጣለሁ? አለ። እርሱም። ይበላሉ ያተርፋሉም ብሎ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው አለ።
44 ፤ እንዲሁም በፊታቸው አኖረው፥ እንደ እግዚአብሔርም ቃል በሉ፥ አተረፉም።