መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25


ምዕራፍ 13

በይሁዳ ንጉሥ በአካዝያስ ልጅ በኢዮአስ በሀያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ አሥራ ሰባትም ዓመት ነገሠ።
2 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፥ እስራኤልንም ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኃጢአት ተከተለ፤ ከእርስዋም አልራቀም።
3 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በዘመኑም ሁሉ በሶርያው ንጉሥ በአዛሄል እጅ፥ በአዛሄልም ልጅ በወልደ አዴር እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር።
4 ፤ ኢዮአካዝም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ያስጨነቀበትን ጭንቀት አይቶአልና ሰማው።
5 ፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታዳጊ ሰጠ፥ ከሶርያውያንም እጅ ዳኑ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ቀድሞው ጊዜ በድንኳናቸው ተቀመጡ።
6 ፤ ነገር ግን በእርስዋ ሄዱ እንጂ እስራኤልን ካሳተው ከኢዮርብዓም ቤት ኃጢአት አልራቁም፤ ደግሞም የማምለኪያ ዐፀድ በሰማርያ ቆሞ ቀረ።
7 ፤ ለኢዮአካዝም ከአምሳ ፈረሰኞች፥ ከአሥርም ሰረገሎች፥ ከአሥር ሺህም እግረኞች በቀር ሕዝብ አልቀረለትም፤ የሶርያ ንጉሥ አጥፍቶአቸዋልና፥ በአውድማም እንዳላ ዕብቅ አድቅቆአቸዋልና።
8 ፤ የቀረውም የኢዮአካዝ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
9 ፤ ኢዮአካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት፤ ልጁም ዮአስ በፋንታው ነገሠ።
10 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ አሥራ ስድስትም ዓመት ነገሠ።
11 ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፋ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን በሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት ሁሉ ሄደ እንጂ ከእርስዋ አልራቀም።
12 ፤ የቀረውም የዮአስ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከይሁዳም ከአሜስያስ ጋር የተዋጋበት ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
13 ፤ ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ ኢዮርብዓምም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ።
14 ፤ ኤልሳዕም በሚሞትበት በሽታ ታመመ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ ወርዶ በፊቱ አለቀሰና። አባቴ ሆይ፥ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች አለ።
15 ፤ ኤልሳዕም። ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ አለው፤ ቀስቱንና ፍላጻዎችንም ወሰደ።
16 ፤ የእስራኤልንም ንጉሥ። እጅህን በቀስቱ ላይ ጫን አለው። እጁንም ጫነበት፤ ኤልሳዕም እጁን በንጉሡ እጅ ላይ ጭኖ።
17 ፤ የምስራቁን መስኮት ክፈት አለ፤ ከፈተውም። ኤልሳዕም። ወርውር አለ፤ ወረወረውም። እርሱም። የእግዚአብሔር መድኃኒት ፍላጻ ነው፤ በሶርያ ላይ የመድኃኒት ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ሶርያዊያንን በአፌቅ ትመታለህ አለ።
18 ፤ ደግሞም። ፍላጻዎቹን ውሰድ አለው፤ ወሰዳቸውም። የእስራኤልንም ንጉሥ። ምድሩን ምታው አለው። ሦስት ጊዜም መትቶ ቆመ።
19 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ተቆጥቶ። አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ኖሮ ሶርያን እስክታጠፋው ድረስ በመታኸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ አለ።
20 ፤ ኤልሳዕም ሞተ፥ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር።
21 ፤ ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፥ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዮው ድኖ በእግሩ ቆመ።
22 ፤ የሶርያም ንጉሥ አዛሄል በኢዮአካዝ ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስጨነቀ፤
23 ፤ እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፥ ማራቸውም፥ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ስላደረገውም ቃል ኪዳን እነርሱን ተመለከተ፤ ሊያጠፋቸውም አልወደደም፥ ፈጽሞም ከፊቱ አልጣላቸውም።
24 ፤ የሶርያም ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁም ወልደ አዴር በፋንታው ነገሠ።
25 ፤ አዛሄልም ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በሰልፍ የወሰዳቸውን ከተሞች የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከአዛሄል ልጅ ከወልደ አዴር እጅ ወሰደ። ዮአስም ሦስት ጊዜ መታው፥ የእስራኤልንም ከተሞች መለሰ።