ምዕራፍ 7

ኤልሳዕም። የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ይሸመታል አለ።
2 ፤ ንጉሡም በእጁ ተደግፎ የነበረ አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? አለው። እርሱም። እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም አለ። ፕ
3 ፤ በበሩም መግቢያ አራት ለምጻም ሰዎች ነበሩ፤ እርስ በርሳቸውም። እስክንሞት ድረስ በዚህ ለምን እንቀመጣለን?
4 ፤ ወደ ከተማ እንገባ ዘንድ ብንወድድ ራብ በከተማ አለ፥ በዚያም እንሞታለን፤ በዚህም ብንቀመጥ እንሞታለን። እንግዲህ ኑ፥ ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሽሽ፤ በሕይወት ቢያኖሩን እንኖራለን፤ ቢገድሉንም እንሞታለን ተባባሉ።
5 ፤ ጨለምለም ባለ ጊዜ ወደ ሶርያውያን ሰፈር ይሄዱ ዘንድ ተነሡ፤ ወደ ሶርያውያንም ሰፈር መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ማንም አልነበረም።
6 ፤ እግዚአብሔር ለሶርያውያን የሰረገላና የፈረስ የብዙም ጭፍራ ድምፅ አሰምቶ ነበር፤ እርስ በርሳቸውም። እነሆ፥ የእስራኤል ንጉሥ የኬጢያውያንና የግብጻውያንን ነገሥት ቀጥሮ አምጥቶብናል ይባባሉ ነበር።
7 ፤ ስለዚህም ተነሥተው በጨለማ ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውንና ፈረሶቻቸውን አህዮቻቸውንና ሰፈሩን እንዳለ ትተው ነፍሳቸውን ያድኑ ዘንድ ሸሹ።
8 ፤ እነዚህም ለምጻሞች ወደ ሰፈሩ መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ገብተው በሉ ጠጡም፥ ከዚያም ወርቅና ብር ልብስም ወሰዱ፥ ሄደውም ሸሸጉት፤ ተመልሰውም ወደ ሌላ ድንኳን ገቡ፥ ከዚያም ደግሞ ወስደው ሸሸጉ።
9 ፤ ከዚያም ወዲያ እርስ በርሳቸው። መልካም አላደረግንም፤ ዛሬ የመልካም ምስራች ቀን ነው፥ እኛም ዝም ብለናል፤ እስኪነጋም ድረስ ብንቆይ በደለኞች እንሆናለን፤ ኑ፥ እንሂድ፤ ለንጉሥ ቤተ ሰብ እንናገር ተባባሉ።
10 ፤ መጥተውም። ወደ ሶርያውያን ሰፈር መጣን፥ እነሆም፥ ፈረሶችና አህዮች ታስረው፥ ድንኳኖችም ተተክለው ነበር እንጂ ሰው አልነበረም፥ የሰውም ድምፅ አልነበረም ብለው ወደ ከተማይቱ ደጅ ጠባቂ ጮኹ።
11 ፤ የደጁም ጠባቂዎች ጠሩ፥ ለንጉሡም ቤት ውስጥ አወሩ።
12 ፤ ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ባሪያዎቹን። ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደ ተራብን ያውቃሉ፤ ስለዚህ። ከከተማይቱ በወጡ ጊዜ በሕይወታቸው እንይዛቸዋለን፥ ወደ ከተማም እንገባለን ብለው በሜዳ ይሸሸጉ ዘንድ ከሰፈሩ ወጥተዋል አላቸው።
13 ፤ ከባሪያዎቹም አንዱ መልሶ። በከተማ ከቀሩት ፈረሶች አምስት ይውሰዱ፤ እነሆ፥ እንደ ቀሩት እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እነሆ፥ እንዳለቁ እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እንስደድም፥ እንይም አለ።
14 ፤ ሁለትም ሰረገሎች ከፈረሶች ጋር ወሰዱ፤ ንጉሡም። ሄዳችሁ እዩ ብሎ ከሶርያውያን ሠራዊት በኋላ ላከ።
15 ፤ በኋላቸው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ሄዱ፤ እነሆም፥ ሶርያውያን ሲሸሹ የጣሉት ልብስና ዕቃ መንገዱን ሁሉ ሞልቶ ነበር። መልእክተኞችም ተመልሰው ለንጉሡ ነገሩት።
16 ፤ ሕዝቡም ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ተሸመተ።
17 ፤ ንጉሡም ያን እጁን ይደግፈው የነበረውን አለቃ በሩን ይጠብቅ ዘንድ አቆመው። ሕዝቡም በበሩ ረገጠው፥ ንጉሡም ወደ እርሱ በወረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው ሞተ።
18 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ለንጉሡ። ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል፥ አንድም መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል ይሸመታል ብሎ እንደ ተናገረው ነገር እንዲሁ ሆነ።
19 ፤ ያም አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? ብሎ ነበር፤ እርሱም። እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም ብሎት ነበር።
20 ፤ እንዲሁም ደረሰበት፤ ሕዝቡም በበሩ ረገጠውና ሞተ።