መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25


ምዕራፍ 25

ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠኝኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠሩባት።
2 ፤ ከተማይቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ድረስ ተከብባ ነበር።
3 ፤ በአራተኛውም ወር በዘጠኝኛው ቀን በከተማይቱ ራብ ጸንቶ ነበርና ለአገሩ ሰዎች እንጀራ ታጣ።
4 ፤ ከተማይቱም ተሰበረች፥ ሰልፈኞችም ሁሉ በሁለት ቅጥር መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ሸሹ፤ ከለዳውያንም በከተማይቱ ዙሪያ ነበሩ፤ በዓረባም መንገድ ሄዱ።
5 ፤ የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከታተሉ፥ በኢያሪኮም ሜዳ ያዙት፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበትነው ነበር።
6 ፤ ንጉሡንም ይዘው የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጡት፤ ፍርድም ፈረዱበት።
7 ፤ የሴዴቅያስንም ልጆች በፊቱ ገደሉአቸው፤ የሴዴቅያስንም ዓይኖች አወጡ፥ በሰንሰለትም አሰሩት፥ ወደ ባቢሎንም ወሰዱት።
8 ፤ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር በአሥራ ዘጠኝኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ባሪያ የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
9 ፤ የእግዚአብሔርንም ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆቹን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ።
10 ፤ ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ዙሪያዋን አፈረሱ።
11 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ ውስጥ የቀረውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የቀሩትንም ሕዝብ አፈለሰ።
12 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ከአገሩ ድሆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ።
13 ፤ ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የነበሩትን የናስ ዓምዶች፥ በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናስ ኵሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ።
14 ፤ ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹንም መኰስተሪያዎቹንና ጭልፋዎቹንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ።
15 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ማንደጃዎቹንና መቀመጨዎቹን፥ የወርቁን ዕቃ ሁሉ በወርቅ፥ የብሩንም በብር አድርጎ ወሰደ።
16 ፤ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት የሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች አንዱንም ኵሬ መቀመጫዎቹንም ወሰደ፤ ለእነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረውም።
17 ፤ የአንዱም ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የናስም ጕልላት ነበረበት፤ የጕልላቱም ርዝመት ሦስት ክንድ ነበረ፥ በጕልላቱም ላይ በዙሪያው የናስ መርበብና ሮማኖች ነበሩ፤ እንዲሁም ደግሞ በሁለተኛው ዓምድ ላይ መርበብ ነበረበት።
18 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን ሁለተኛውንም ካህን ሶፎንያስን ሦስቱንም በረኞች ወሰደ።
19 ፤ ከከተማይቱም በሰልፈኞች ላይ ተሾመው ከነበሩት አንዱን ጃንደረባ፥ በከተማይቱም የተገኙትን በንጉሡ ፊት የሚቆሙትን አምስቱን ሰዎች፥ የአገሩንም ሕዝብ የሚያሰልፍ የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ፥ በከተማይቱም ከተገኙት ከአገሩ ሕዝብ ስድሳ ሰዎች ወሰደ።
20 ፤ የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ወስዶ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጣቸው።
21 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፥ በሐማትም ምድር ባለችው በሪብላ ገደላቸው። እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ።
22 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ምድር በቀረው ሕዝብ ላይ የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን አለቃ አደረገው።
23 ፤ የጭፍሮቹም አለቆች ሁሉ፥ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፥ የነጦፋዊውም የተንሑሜት ልጅ ሠራያ፥ የማዕካታዊውም ልጅ ያእዛንያ፥ ሰዎቻቸውም የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያስን እንደ ሾመ በሰሙ ጊዜ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ።
24 ፤ ጎዶልያስም። ከከለዳውያን ሎሌዎች የተነሣ አትፍሩ፥ በአገሩ ተቀመጡ፥ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፥ መልካምም ይሆንላችኋል ብሎ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው ማለላቸው።
25 ፤ በሰባተኛው ወር ግን የመንግሥት ዘር የነበረ የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር አሥር ሰዎች መጥተው ጎዶልያስንና ከእርሱ ጋር በምጽጳ የነበሩትን አይሁድንና ከለዳውያንን እስኪሞቱ ድረስ መቱአቸው።
26 ፤ ከለዳውያንንም ፈርተው ነበርና ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡ ሁሉ የጭፍሮቹም አለቆች ተነሥተው ወደ ግብጽ መጡ።
27 ፤ እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማከረ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ዮርማሮዴቅ በነገሠ በአንደኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪንን ከወህኒ አወጣው፤
28 ፤ በፍቅርም ተናገረው፥ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት።
29 ፤ በወህኒም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠለት፤ ዮአኪንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በፊቱ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር።
30 ፤ ንጉሡም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ የዘወትር ቀለብ ዕለት ዕለት ይሰጠው ነበር።