ኦሪት ዘኍልቍ
ምዕራፍ 9
ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሲና ምድረ በዳ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ የእስራኤል ልጆች በጊዜው ፋሲካውን ያድርጉ፤
3 ፤ በዚህ ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በጊዜው አድርጉት፤ እንደ ሥርዓቱ ሁሉ እንደ ፍርዱም ሁሉ አድርጉት።
4 ፤ ሙሴም ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ተናገራቸው።
5 ፤ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካን አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ።
6 ፤ በሞተ ሰው ሬሳ የረከሱ ሰዎችም ነበሩ፥ ስለዚህም በዚያ ቀን ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ አልቻሉም። በዚያም ቀን ወደ ሙሴና ወደ አሮን ቀረቡ።
7 ፤ እነዚያም ሰዎች። በሞተ ሰው ሬሳ ረክሰናል፤ በእስራኤል ልጆች መካከል በጊዜው ቍርባን ለእግዚአብሔር እንዳናቀርብ ስለ ምን እንከለከላለን? አሉት።
8 ፤ ሙሴም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስክሰማ ድረስ ቈዩ አላቸው።
9 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
10 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእናንተ ወይም ከትውልዶቻችሁ ዘንድ ሰው በሬሳ ቢረክስ፥ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ፥ እርሱ ደግሞ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያድርግ።
11 ፤ በሁለተኛው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ያድርጉት፤ ከቂጣ እንጀራና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት።
12 ፤ ከእርሱም እስከ ነገ ምንም አያስቀሩ፥ ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ፤ እንደ ፋሲካ ሥርዓት ሁሉ ያድርጉት።
13 ፤ ነገር ግን ንጹሕ የሆነ ሰው በመንገድም ላይ ያልሆነ ፋሲካን ባያደርግ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ የእግዚአብሔርን ቍርባን በጊዜው አላቀረበምና ያ ሰው ኃጢአቱን ይሸከማል።
14 ፤ በመካከላችሁም መጻተኛ ቢኖር፥ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያደርግ ዘንድ ቢወድድ፥ እንደ ፋሲካ ሥርዓት እንደ ፍርዱም እንዲሁ ያድርግ፤ ለመጻተኛና ለአገር ልጅ አንድ ሥርዓት ይሁንላችሁ።
15 ፤ ማደሪያውም በተተከለ ቀን ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከማታም ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ በማደሪያው ላይ እንደ እሳት ይመስል ነበር።
16 ፤ እንዲሁ ሁልጊዜ ነበረ፤ በቀን ደመና በሌሊትም የእሳት አምሳል ይሸፍነው ነበር።
17 ፤ ደመናውም ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም በቆመበት ስፍራ በዚያ የእስራኤል ልጆች ይሰፍሩ ነበር።
18 ፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር። ደመናው በማደሪያው ላይ በተቀመጠበት ዘመን ሁሉ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር።
19 ፤ ደመናውም በማደሪያው ላይ ብዙ ቀን በተቀመጠ ጊዜ የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር።
20 ፤ አንዳንድ ጊዜ ደመናው ጥቂት ቀን በማደሪያው ላይ ይሆን ነበር፤ በዚያን ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፤ እንደ እግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር።
21 ፤ አንዳንድ ጊዜም ደመናው ከማታ ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ ይቀመጥ ነበር፤ በጥዋትም ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር፤ በቀንም በሌሊትም ቢሆን፥ ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር።
22 ፤ ደመናውም ሁለት ቀን ወይም አንድ ወር ወይም አንድ ዓመት ቆይቶ በማደሪያው ላይ ቢቀመጥ የእስራኤል ልጆች በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር፤ ነገር ግን በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር።
23 ፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር፥ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።