ምዕራፍ 5

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ የእስራኤል ልጆች ለምጻሙን ሁሉ፥ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ፥ በሬሳም የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው፤
3 ፤ ወንዱንና ሴቱን አውጡ፤ እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈሩ አውጡአቸው።
4 ፤ የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ ከሰፈሩ አወጡአቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ።
5 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
6 ፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። ወንድ ወይም ሴት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይተላለፍ ዘንድ ሰው የሚሠራውን ኃጢአት ቢሠራ፥ በዚያም ሰው ላይ በደል ቢሆን፥ በሠራው ኃጢአት ይናዘዝ፤
7 ፤ የወሰደውንም በሙሉ ይመልስ አምስተኛውንም ይጨምርበት፥ ለበደለውም ሰው ይስጠው።
8 ፤ ነገር ግን ይመልስለት ዘንድ ሰውዮው ዘመድ ባይኖረው፥ ስለ በደል ለእግዚአብሔር የሚመልሰው ነገር ለካህኑ ይሁን፥ ይህም ስለ እርሱ ማስተሰረያ ከሚደረግበት አውራ በግ በላይ ይጨመር።
9 ፤ የእስራኤልም ልጆች ለካህኑ የሚያቀርቡት የተቀደሰ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለእርሱ ይሁን።
10 ፤ የተቀደሰ የሰው ነገር ሁሉ፥ ሰውም ለካህኑ የሚሰጠው ሁሉ ለእርሱ ይሁን።
11 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
12 ፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። የማንኛውም ሰው ሚስት ከእርሱ ፈቀቅ ብትል፥ በእርሱም ላይ ብትበድል፥
13 ፤ ከሌላም ሰው ጋር ብትተኛ፥ ከባልዋም ዓይን ቢሸሸግ፥ እርስዋም ተሰውራ ብትረክስ፥ ምስክርም ባይኖርባት፥ በምንዝርም ባትገኝ፥
14 ፤ በባልዋም ላይ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ እርስዋም ስትረክስ ስለ ሚስቱ ቢቀና፤ ወይም እርስዋ ሳትረክስ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፤
15 ፤ ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፥ የኢፍ መስፈሪያም አሥረኛ እጅ ገብስ ዱቄት ቍርባን ስለ እርስዋ ያምጣ፤ የቅንዓት ቍርባን ነውና፥ ኃጢአትንም የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና ዘይት አያፍስስበት፥ ዕጣንም አይጨምርበት።
16 ፤ ካህኑም ያቀርባታል በእግዚአብሔርም ፊት ያቆማታል፤
17 ፤ ካህኑም የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ዕቃ ይወስዳል፤ ካህኑም በማደሪያው ውስጥ ካለው ትቢያ ወስዶ በውኃ ላይ ይረጨዋል፤
18 ፤ ካህኑም ሴቲቱን በእግዚአብሔር ፊት ያቆማታል፥ የሴቲቱንም ራስ ይገልጣል፥ በእጅዋም ለመታሰቢያ የሚሆነውን የእህል ቍርባን፥ ለቅንዓት ቍርባን፥ ያኖራል፤ በካህኑም እጅ እርግማንን የሚያመጣው መራራ ውኃ ይሆናል።
19 ፤ ካህኑም ያምላታል፥ ሴቲቱንም እንዲህ ይላታል። ሌላ ወንድ አልተኛሽ፥ ባልሽንም አልተውሽ፥ ራስሽንም አላረከስሽ እንደ ሆነ፥ እርግማንን ከሚያመጣ ከዚህ መራራ ውኃ ንጹሕ ሁኚ፤
20 ፤ ነገር ግን ባልሽን ትተሽ ረክሰሽ እንደ ሆነ፥ ከባልሽም ሌላ ከወንድ ጋር ተኝተሽ እንደሆነ፤
21 ፤ ካህኑም ሴቲቱን በመርገም መሐላ ያምላታል፥ ካህኑም ሴቲቱን። እግዚአብሔር ጭንሽን እያሰለሰለ ሆድሽንም እየነፋ፥ እግዚአብሔር ለመርገምና ለመሐላ በሕዝብሽ መካከል ያድርግሽ፤
22 ፤ እርግማንንም የሚያመጣ ይህ ውኃ ወደ ሆድሽ ይግባ፥ ሆድሽንም ይንፋው፥ ጭንሽንም ያበስብሰው ይላታል፤ ሴቲቱም። አሜን አሜን ትላለች።
23 ፤ ካህኑም እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ይጽፈዋል፥ በመራራውም ውኃ ይደመስሰዋል፤
24 ፤ እርግማን የሚያመጣውንም መራራ ውኃ ለሴቲቱ ይጠጣታል፤ የእርግማኑም ውኃ በገባባት ጊዜ መራራ ይሆናል።
25 ፤ ካህኑም የቅንዓቱን የእህል ቍርባን ከሴቲቱ እጅ ይወስዳል፥ የእህሉንም ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል፥ ወደ መሠዊያውም ያመጣዋል፤
26 ፤ ካህኑም ከእህሉ ቍርባን አንድ እፍኝ ሙሉ ለመታሰቢያው ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፥ ከዚያም በኋላ ለሴቲቱ ውኃውን ያጠጣታል።
27 ፤ ውኃውን ካጠጣት በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ ረክሳና በባልዋ ላይ አመንዝራ እንደ ሆነች፥ እርግማንን የሚያመጣው ውኃ ገብቶ መራራ ይሆንባታል፥ ሆድዋም ይነፋል፥ ጭንዋም ይሰለስላል፤ ሴቲቱም በሕዝብዋ መካከል ለመርገም ትሆናለች።
28 ፤ ያልረከሰች ያለ ነውርም እንደ ሆነች፥ ንጹሕ ትሆናለች፥ ልጆችንም ታረግዛለች።
29
30 ፤ ሴት ባልዋን ትታ በረከሰች ጊዜ፥ ወይም በሰው ላይ የቅንዓት መንፈስ በመጣበት ጊዜ፥ ስለ ሚስቱም በቀና ጊዜ፥ የቅንዓት ሕግ ይህ ነው፤ ሴቲቱንም በእግዚአብሔር ፊት ያቁማት፥ ካህኑም እንደዚህ ሕግ ሁሉ ያድርግባት።
31 ፤ ሰውዮውም ከኃጢአት ንጹሕ ይሆናል፥ ሴቲቱም ኃጢአትዋን ትሸከማለች።