ምዕራፍ 27

ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ወገኖች፥ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጅ የኦፌር ልጅ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ቀረቡ፤ የእነዚህም ሴቶች ልጆች ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ።
2 ፤ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በሙሴና በካህኑ በአልዓዛር በአለቆቹም በማኅበሩም ሁሉ ፊት ቆመው።
3 ፤ አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ በራሱ ኃጢአት ሞተ እንጂ ከቆሬ ጋር በእግዚአብሔር ላይ በተሰበሰቡ ወገን መካከል አልነበረም፤ ወንዶችም ልጆች አልነበሩትም።
4 ፤ ወንድ ልጅስ ባይኖረው የአባታችን ስም ከወገኑ መካከል ለምን ይጠፋል? በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስትን ስጠን አሉ።
5 ፤ ሙሴም ነገራቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
7 ፤ የሰለጰዓድ ልጆች እውነት ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ለእነርሱ አሳልፈህ ስጥ።
8 ፤ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ሰው ቢሞት ወንድ ልጅም ባይኖረው፥ ርስቱ ለሴት ልጁ ይለፍ፤
9 ፤ ሴት ልጅም ባትኖረው ርስቱን ለወንድሞቹ ስጡ፤
10 ፤ ወንድሞችም ባይኖሩት ርስቱን ለአባቱ ወንድሞች ስጡ፤
11 ፤ የአባቱም ወንድሞች ባይኖሩት ከወገኑ ለቀረበ ዘመድ ርስቱን ስጡ እርሱም ይውረሰው፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ለእስራኤል ልጆች ሥርዓትና ፍርድ ይሁን።
12 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደዚህ ወደ ዓባሪም ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች የሰጠኋትን ምድር እይ፤
13 ፤ ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን እንደ ተከማቸ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትከማቻለህ።
14 ፤ እናንተ በጺን ምድረ በዳ በማኅበሩ ጠብ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አልቀደሳችሁኝምና። ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የመሪባ ውኃ ነው።
15 ፤ ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
16
17 ፤ የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን፥ በፊታቸው የሚወጣውን በፊታቸውም የሚገባውን የሚያስወጣቸውንም የሚያስገባቸውንም ሰው የሥጋ ሁሉ መንፈስ አምላክ እግዚአብሔር በማኅበሩ ላይ ይሹመው።
18 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። መንፈስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤
19 ፤ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቁመው፥ እነርሱም እያዩ እዘዘው።
20 ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ አኑርበት።
21 ፤ በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በኡሪም ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፥ በቃሉም ይግቡ።
22 ፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤
23 ፤ እግዚአብሔርም በሙሴ እንደ ተናገረ፥ እጁን በላዩ ጫነበት፥ አዘዘውም።