ምዕራፍ 17

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፥ ከእነርሱም ከእያንዳንዱ ከየአባቶቻቸው ቤት አንድ አንድ በትር፥ ከአለቆቻቸው ከየአባቶቻቸው ቤት አሥራ ሁለት በትሮች፥ ውሰድ፤ የእያንዳንዱንም ስም በየበትሩ ላይ ጻፍ።
3 ፤ አንድ በትርም ለአባቶቻቸው ቤት አለቃ ይሆናልና በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ።
4 ፤ እኔ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት አኑራቸው።
5 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ የመረጥሁት ሰው በትር ታቈጠቁጣለች፤ በእናንተም ላይ የሚያጕረመርሙባችሁን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ።
6 ፤ ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ አለቆቻቸው ሁሉ አሥራ ሁለት በትሮች፥ እያንዳንዱም አለቃ በየአባቱ ቤት አንድ አንድ በትር፥ ሰጡት፤ የአሮንም በትር በበትሮቻቸው መካከል ነበረች።
7 ፤ ሙሴም በትሮቹን በእግዚአብሔር ፊት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ አኖራቸው።
8 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ፤ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቈጠቈጠች፥ ለመለመችም፥ አበባም አወጣች፥ የበሰለ ለውዝም አፈራች።
9 ፤ ሙሴም በትሮችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አወጣቸው፤ እነርሱም አዩ፥ እያንዳንዱም በትሩን ወሰደ።
10 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የአሮንን በትር ወደ ምስክሩ ፊት መልስ፤ ማጕረምረማቸው ከእኔ ዘንድ እንዲጠፋ እነርሱም እንዳይሞቱ ለሚያምፁብኝ ልጆች ምልክት ሆና ትጠበቅ አለው።
11 ፤ ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።
12 ፤ የእስራኤልም ልጆች ሙሴን።እነሆ፥ እንሞታለን፥ እንጠፋለን፥ ሁላችንም እንጠፋለን።
13 ፤ የሚቀርብ ሁሉ፥ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ የሚቀርብ፥ ይሞታል፤ በውኑ ሁላችን እንሞታለንን? ብለው ተናገሩት።