ምዕራፍ 33

የእስራኤልም ልጆች ጕዞ ከሙሴና ከአሮን እጅ በታች በጭፍሮቻቸው ከግብፅ በወጡ ጊዜ እንዲህ ነበረ።
2 ፤ ሙሴም በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ጕዞአቸው አወጣጣቸውን ጻፈ፤ እንደ አወጣጣቸውም ጕዞአቸው እንዲህ ነበረ።
3 ፤ በመጀመሪያው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን ከራምሴ ተጓዙ፤ ከፋሲካ በኋላ በነጋው የእስራኤል ልጆች ግብፃውያን ሁሉ እያዩ ከፍ ባለች እጅ ወጡ።
4 ፤ በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው።
5 ፤ የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተጕዘው በሱኮት ሰፈሩ።
6 ፤ ከሱኮትም ተጕዘው በምድረ በዳ ዳርቻ ባለች በኤታም ሰፈሩ።
7 ፤ ከኤታምም ተጕዘው በበኣልዛፎን ፊት ወደ ነበረች ወደ ፊሀሒሮት ተመለሱ፤ በሚግዶልም ፊት ለፊት ሰፈሩ።
8 ፤ ከፊሀሒሮትም ተጕዘው በባሕሩ ውስጥ ወደ ምድረ በዳ አለፉ፤ በኤታምም በረሀ የሦስት ቀን መንገድ ሄደው በማራ ሰፈሩ።
9 ፤ ከማራም ተጕዘው ወደ ኤሊም መጡ፤ በኤሊምም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮች ሰባ ዘንባቦችም ነበሩ፤ በዚያም ሰፈሩ።
10 ፤ ከኤሊምም ተጕዘው በኤርትራ ባሕር ዳር ሰፈሩ።
11 ፤ ከኤርትራም ባሕር ተጕዘው በሲን ምድረ በዳ ሰፈሩ።
12 ፤ ከሲን ምድረ በዳም ተጕዘው በራፋቃ ሰፈሩ።
13 ፤ ከራፋቃም ተጕዘው በኤሉስ ሰፈሩ።
14 ፤ ከኤሉስም ተጕዘው በራፊዲም ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም።
15 ፤ ከራፊዲምም ተጕዘው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ።
16 ፤ ከሲናም ምድረ በዳ ተጕዘው በምኞት መቃብር ሰፈሩ።
17 ፤ ከምኞት መቃብርም ተጕዘው በሐጼሮት ሰፈሩ።
18 ፤ ከሐጼሮትም ተጕዘው በሪትማ ሰፈሩ።
19 ፤ ከሪትማም ተጕዘው በሬሞን ዘፋሬስ ሰፈሩ።
20 ፤ ከሬሞን ዘፋሬስም ተጕዘው በልብና ሰፈሩ።
21 ፤ ከልብናም ተጕዘው በሪሳ ሰፈሩ።
22 ፤ ከሪሳም ተጕዘው በቀሄላታ ሰፈሩ።
23 ፤ ከቀሄላታም ተጕዘው በሻፍር ተራራ ሰፈሩ።
24 ፤ ከሻፍር ተራራም ተጕዘው በሐራዳ ሰፈሩ።
25 ፤ ከሐራዳም ተጕዘው በመቅሄሎት ሰፈሩ።
26 ፤ ከመቅሄሎትም ተጕዘው በታሐት ሰፈሩ።
27 ፤ ከታሐትም ተጕዘው በታራ ሰፈሩ።
28 ፤ ከታራም ተጕዘው በሚትቃ ሰፈሩ።
29 ፤ ከሚትቃም ተጕዘው በሐሽሞና ሰፈሩ።
30 ፤ ከሐሽሞናም ተጕዘው በሞሴሮት ሰፈሩ።
31 ፤ ከሞሴሮትም ተጕዘው በብኔያዕቃን ሰፈሩ።
32 ፤ ከብኔያዕቃንም ተጕዘው በሖርሃጊድጋድ ሰፈሩ።
33 ፤ ከሖርሃጊድጋድም ተጕዘው በዮጥባታ ሰፈሩ።
34 ፤ ከዮጥባታም ተጕዘው በዔብሮና ሰፈሩ።
35 ፤ ከዔብሮናም ተጕዘው በዔጽዮንጋብር ሰፈሩ።
36 ፤ ከዔጽዮንጋብርም ተጕዘው በጺን ምድረ በዳ ሰፈሩ፤ ይህችም ቃዴስ ናት።
37 ፤ ከቃዴስም ተጕዘው በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ።
38 ፤ ካህኑም አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ሖር ተራራ ላይ ወጣ፥ በዚያም የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በአርባኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ።
39 ፤ አሮንም በሖር ተራራ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ሦስት ዓመት ነበር።
40 ፤ በከነዓን ምድርም በደቡብ በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ የእስራኤል ልጆች እንደ መጡ ሰማ።
41 ፤ እነርሱም ከሖር ተራራ ተጕዘው በሴልሞና ሰፈሩ።
42 ፤ ከሴልሞናም ተጕዘው በፉኖን ሰፈሩ።
43 ፤ ከፉኖንም ተጕዘው በኦቦት ሰፈሩ።
44 ፤ ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ዳርቻ ባለው በጋይ ሰፈሩ።
45 ፤ ከጋይም ተጕዘው በዲቦንጋድ ሰፈሩ።
46 ፤ ከዲቦንጋድም ተጕዘው በዓልሞንዲብላታይም ሰፈሩ።
47 ፤ ከዓልሞንዲብላታይምም ተጕዘው በናባው ፊት ባሉ በዓብሪም ተራሮች ላይ ሰፈሩ።
48 ፤ ከዓብሪምም ተራሮች ተጕዘው በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ባለው በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ።
49 ፤ በዮርዳኖስም አጠገብ በሞዓብ ሜዳ ላይ ከቤትየሺሞት እስከ አቤልሰጢም ድረስ ሰፈሩ።
50 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
51 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥
52 ፤ የአገሩን ሰዎች ሁሉ ከፊታችሁ ታሳድዳላችሁ፥ የተቀረጹትንም ድንጋዮቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ በኮረብታ ላይ ያሉትን መስገጃዎቻቸውንም ታፈርሳላችሁ፤
53 ፤ ምድሪቱንም ለእናንተ ርስት አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁና ምድሪቱን ትወርሱአታላችሁ ትቀመጡባታላችሁም።
54 ፤ ምድሪቱንም በየወገኖቻችሁ በዕጣ ትወርሳላችሁ፤ ለብዙዎች እንደ ብዛታቸው ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣላችሁ፤ እያዳንዱ ሁሉ ዕጣ እንደ ወደቀለት በዚያ ርስቱ ይሆናል፤ በየአባቶቻችሁ ነገዶች ትወርሳላችሁ።
55 ፤ የአገሩንም ሰዎች ከፊታችሁ ባታሳድዱ፥ ያስቀራችኋቸው ለዓይናችሁ እንደ እሾህ ለጎናችሁም እንደሚወጋ ነገር ይሆኑባችኋል፥ በምትቀመጡባትም ምድር ያስጨንቁአችኋል።
56 ፤ እኔም በእነርሱ አደርገው ዘንድ ያሰብሁትን በእናንተ አደርግባችኋለሁ።