ምዕራፍ 30

ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ነገዶች አለቆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው።
2 ፤ ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል፥ ወይም ራሱ በመሐላ ቢያስር፥ ቃሉን አይስበር፤ ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ።
3 ፤ ሴትም ደግሞ ለእግዚአብሔር ስእለት ብትሳል፥ እርስዋም በአባትዋ ቤት ሳለች በብላቴንነትዋ ጊዜ ራስዋን በመሐላ ብታስር፥
4 ፤ አባትዋም ራስዋን ያሰረችበትን መሐላ ስእለትዋንም ቢሰማ፥ አባትዋም ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ሁሉ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል።
5 ፤ አባትዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላዋ አይጸኑም፤ አባትዋ ከልክሎአታልና እግዚአብሔር ይቅር ይላታል።
6 ፤ በተሳለችም ጊዜ ራስዋንም በመሐላ ያሰረችበት ነገር ከአፍዋ በወጣ ጊዜ ባል ያገባች ብትሆን፥
7 ፤ ባልዋም ቢሰማ፥ በሰማበትም ቀን ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸናል።
8 ፤ ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ በእርስዋ ላይ ያለውን ስእለትዋን ራስዋንም በመሐላ ያሰረችበትን የአፍዋን ነገር ከንቱ ያደርገዋል፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል።
9 ፤ ባልዋ የሞተባት ወይም የተፋታች ግን ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸኑባታል።
10 ፤ ሴትም በባልዋ ቤት ሳለች ብትሳል፥ ወይም ራስዋን በመሐላ ብታስር፥
11 ፤ ባልዋም ሰምቶ ዝም ቢላት ባይከለክላትም፥ ስእለትዋ ሁሉ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል።
12 ፤ ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ከንቱ ቢያደርገው፥ ስለ ስእለትዋ ወይም ራስዋን ስላሰረችበት መሐላ ከአፍዋ የወጣው ነገር አይጸናም፤ ባልዋ ከንቱ አድርጎታል፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል።
13 ፤ ስእለትዋን ሁሉ ነፍስዋንም የሚያዋርደውን መሐላ ሁሉ ባልዋ ያጸናዋል፥ ባልዋም ከንቱ ያደርገዋል።
14 ፤ ባልዋ ግን በየዕለቱ ዝም ቢላት፥ ስእለትዋን ሁሉ በእርስዋም ላይ ያለውን መሐላ ሁሉ አጽንቶታል፤ በሰማበት ቀን ዝም ብሎአታልና አጽንቶታል።
15 ፤ ከሰማው በኋላ ግን ከንቱ ቢያደርገው ኃጢአትዋን ይሸከማል።
16 ፤ እርስዋ በብላቴንነትዋ ጊዜ በአባትዋ ቤት ሳለች በአባትና በልጂቱ መካከል፥ ወይም በባልና በሚስት መካከል ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው ሥርዓት ይህ ነው።