ምዕራፍ 24

በለዓምም እግዚአብሔር እስራኤልን ይባርክ ዘንድ እንዲወድድ ባየ ጊዜ፥ አስቀድሞ ያደርግ የነበረውን አስማት ይሻ ዘንድ አልሄደም፤ ነገር ግን ወደ ምድረ በዳ ፊቱን አቀና።
2 ፤ በለዓምም ዓይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዱ ተቀምጦ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ መጣ።
3 ፤ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤
4 ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል።
5 ፤ ያዕቆብ ሆይ፥ ድንኳኖችህ፥ እስራኤል ሆይ ማደሪያዎችህ ምንኛ ያምራሉ!
6 ፤ እንደ ሸለቆች፥ በወንዝ ዳር እንዳሉ አትክልቶች፥ እግዚአብሔር እንደ ተከለው እሬት በውኃም ዳር እንዳሉ ዝግባዎች ተዘርግተዋል።
7 ፤ ከማድጋዎቹ ውኃ ይፈስሳል፥ ዘሩም በብዙ ውኆች ይሆናል፥ ንጉሡም ከአጋግ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፥ መንግሥቱም ይከበራል።
8 ፤ እግዚአብሔርም ከግብፅ አውጥቶታል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው፤ ጠላቶቹን አሕዛብን ይበላል፥ አጥንቶቻቸውንም ይሰባብራል፥ በፍላጾቹም ይወጋቸዋል።
9 ፤ እንደ አንበሳ ዐርፎ ተኝቶአል፥ እንደ እንስቲቱም አንበሳ ተጋድሞአል፤ ማን ያስነሣዋል? የሚመርቅህ ሁሉ የተመረቀ ይሁን፥ የሚረግምህም ሁሉ የተገመ ይሁን።
10 ፤ የባላቅም ቍጣ በበለዓም ላይ ነደደ፤ እጆቹንም አጨበጨበ፤ ባላቅም በለዓምን። ጠላቶቼን ትረግም ዘንድ ጠራሁህ፥ እነሆም፥ ሦስት ጊዜ ፈጽመህ መረቅሃቸው፤ አሁንም እንግዲህ ወደ ስፍራህ ሽሽ፤
11 ፤ እኔ አከብርህ ዘንድ ወድጄ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን፥ እነሆ፥ ክብርህን ከለከለ አለው።
12
13 ፤ በለዓምም ባላቅን አለው። ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ መልካሙን ወይም ክፉውን ከልቤ ለማድረግ የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ እግዚአብሔር የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ ብዬ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞች አልተናገርኋቸውምን?
14 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ።
15 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤
16 ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል።
17 ፤ አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር ይነሣል፥ የሞዓብንም ማዕዘኖች ይመታል፥ የሤትንም ልጆች ያጠፋል።
18 ፤ ኤዶምያስም ርስቱ ይሆናል፥ ጠላቱ ሴይር ደግሞ ርስቱ ይሆናል፤ እስራኤልም በኃይል ያደርጋል።
19 ፤ ከያዕቆብም የሚወጣ ገዥ ይሆናል፥ ከከተማውም የቀሩትን ያጠፋል።
20 ፤ አማሌቅንም አይቶ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። አማሌቅ የአሕዛብ አለቃ ነበረ፤ ፍጻሜው ግን ወደ ጥፋት ይመጣል።
21 ፤ ቄናውያንንም አይቶ ምሳሌውን ይምስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ማደሪያህ የጸና ነው፥ ጎጆህም በአምባ ላይ ተሠርቶአል፤
22 ፤ ነገር ግን አሦር እስኪማርክህ ድረስ ቄናዊው ለጥፋት ይሆናል።
23 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግ አወይ! ማን በሕይወት ይኖራል?
24 ፤ ከኪቲም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፥ አሦርንም ያስጨንቃሉ፥ ዔቦርንም ያስጨንቃሉ፤ እርሱም ደግሞ ወደ ጥፋት ይመጣል።
25 ፤ በለዓምም ተነሣ፥ ተመልሶም ወደ ስፍራው ሄደ፤ ባላቅም ደግሞ መንገዱን ሄደ።