ምዕራፍ 18

እግዚአብሔርም አሮንን አለው። አንተ ከአንተም ጋር ልጆችህና የአባቶችህ ቤት የመቅደስን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፤ አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ የክህነታችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ።
2 ፤ ደግሞም የአባትህን የሌዊን ነገድ ወንድሞችህን ከአንተ ጋር አቅርብ፤ ከአንተም ጋር በአንድነት ይሁኑ፥ ያገልግሉህም፤ አንተ ግን ከአንተም ጋር ልጆችህ በምስክሩ ድንኳን ፊት ትሆናላችሁ።
3 ፤ እነርሱም ትእዛዝህን የድንኳኑንም ሁሉ አገግሎት ይጠብቁ፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ፥ እናንተም ደግሞ ከእነርሱ ጋር እንዳትሞቱ፥ እነርሱ ወደ መቅደሱ ዕቃና ወደ መሠዊያው አይቅረቡ።
4 ፤ ነገር ግን ከእናንተ ጋር በአንድነት ይሁኑ፥ ለድንኳኑም አገልግሎት ሁሉ የመገናኛውን ድንኳን ይጠብቁ፤ ሌላም ሰው ወደ እናንተ አይቅረብ።
5 ፤ እንደ ገና በእስራኤል ልጆች ላይ ቍጣ እንዳይሆንባቸው እናንተ መቅደሱንና መሠዊያውን ጠብቁ።
6 ፤ እኔም፥ እነሆ፥ ሌዋውያንን ወንድሞቻችሁን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤ የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያደርጉ ዘንድ ለእግዚአብሔር የተሰጡ ለእናንተ ስጦታ ናቸው።
7 ፤ አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ ለመሠዊያው ሥራ የሚሆነውን ሁሉ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የሚሆነውን ታደርጉ ዘንድ ክህነታችሁን ጠብቁ፥ አገልግሉም፤ ክህነቱን ለስጦታ አገልግሎት ሰጥቼአችኋለሁ፤ ሌላም ሰው ቢቀርብ ይገደል።
8 ፤ እግዚአብሔርም አሮንን ተናገረው እንዲህም አለው። እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የቀደሱትን የማንሣት ቍርባኔን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ፤ ስለ መቀባትህ ለአንተና ለልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ።
9 ፤ በእሳት ከሚቀርበው ከተቀደሰው ይህ ለአንተ ይሆናል፤ ለእኔ የሚያመጡት መባቸው ሁሉ፥ የእህሉ ቍርባናቸው ሁሉ፥ የኃጢአታቸውም መስዋዕት ሁሉ፥ የበደላቸውም መሥዋዕት ሁሉ፥ ለአንተ ለልጆችህም የተቀደሰ ይሆናል።
10 ፤ በተቀደሰ ስፍራ ብላው፤ ወንዶች ሁሉ ይብሉት፤ የተቀደሰ ይሆንልሃል።
11 ፤ ይህም ለአንተ ነው፤ የእስራኤል ልጆች ለስጦታ ያቀረቡትን የማንሣትና የመወዝወዝ ቍርባን ሁሉ ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው።
12 ፤ ለእግዚአብሔር ከሚሰጡት የፍሬ መጀመሪያ ከዘይትና ከወይን ከእህልም የተመረጠውን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።
13 ፤ ወደ እግዚአብሔር የሚያመጡት በምድራቸው ያለው ሁሉ የፍሬ መጀመሪያ ለአንተ ይሆናል፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው።
14 ፤ በእስራኤል ዘንድ እርም የሆነው ሁሉ ለአንተ ይሆናል።
15 ፤ ከሰው ወይም ከእንስሳ ቢሆን፥ ለእግዚአብሔር ከሚያቀርቡት ሥጋ ሁሉ ማኅፀን የሚከፍት ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰውን በኵራት ፈጽሞ ትቤዠዋለህ፥ ያልነጻውንም እንስሳ በኵራት ትቤዠዋለህ።
16 ፤ ከአንድ ወር ጀምሮ የምትቤዠውን እንደ ግምትህ ትቤዠዋለህ፤ ግምቱም እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን አምስት ሰቅል ይሆናል፤ እርሱም ሀያ አቦሊ ነው።
17 ፤ ነገር ግን የላም በኵራት ወይም የበግ በኵራት ወይም የፍየል በኵራት አትቤዥም፤ የተቀደሱ ናቸው፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ ትረጨዋለህ፥ ስባቸውንም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለእሳት ቍርባን ታቃጥለዋለህ።
18 ፤ ሥጋቸውም ለአንተ ይሆናል፤ እንደ መወዝወዝ ፍርምባ እንደ ቀኙም ወርች ለአንተ ይሆናል።
19 ፤ የእስራኤል ልጆች ከተቀደሰው ነገር ሁሉ አንሥተው ለእግዚአብሔር ያቀረቡትን ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ለአንተ ከአንተም ጋር ለዘርህ የጨው ቃል ኪዳን ለዘላለም ነው።
20 ፤ እግዚአብሔርም አሮንን አለው። በምድራቸው ርስት በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንልህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ።
21 ፤ ለሌዊም ልጆች፥ እነሆ፥ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ፥ የእስራኤልን ልጆች አሥራት ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ።
22 ፤ ከዚህም በኋላ ኃጢአትን እንዳይሸከሙ እንዳይሞቱም፥ የእስራኤል ልጆች ወደ መገናኛው ድንኳን አይቅረቡ።
23 ፤ ሌዋውያን ግን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ይሥሩ፥ እነርሱም ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ፤ ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም።
24 ፤ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን የሚያቀርቡትን የእስራኤልን ልጆች አሥራት ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ፤ ስለዚህ። በእስራኤል ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም አልኋቸው።
25 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
26 ፤ ለሌዋውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእስራኤል ልጆች ለእናንተ ርስት አድርጌ የሰጠኋችሁን አሥራት በተቀበላችሁ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን የአሥራት አሥራት ታቀርባላችሁ።
27 ፤ የማንሣት ቍርባናችሁም እንደ አውድማው እህልና እንደ ወይን መጭመቂያው ፍሬ ይቈጠርላችኋል።
28 ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ከእስራኤል ልጆች ከምትቀበሉት አሥራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ታቀርባላችሁ፤ የእግዚአብሔርንም የማንሣት ቍርባን ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ።
29 ፤ ከምትቀበሉት ስጦታ ሁሉ፥ ከተመረጠው ከተቀደሰውም ድርሻ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን የማንሣት ቍርባን ሁሉ ታቀርባላችሁ።
30 ፤ ስለዚህ ትላቸዋለህ። ከእርሱ የተመረጠውን ባነሣችሁ ጊዜ እንደ አውድማው እህልና እንደ ወይን መጭመቂያው ፍሬ ለሌዋውያን ይቈጠራል።
31 ፤ እናንተም ቤተ ሰቦቻችሁም፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የማገልገላችሁ ዋጋ ነውና በሁሉ ስፍራ ትበሉታላችሁ።
32 ፤ የተመረጠውንም ከእርሱ ባነሣችሁ ጊዜ ስለ እርሱ ኃጢአትን አትሸከሙም፤ እንዳትሞቱም የእስራኤል ልጆች የቀደሱትን አታረክሱም።