ምዕራፍ 19

እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2 ፤ እግዚአብሔር ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር ያመጡልህ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው።
3 ፤ እርስዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርስዋንም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወስዳታል፥ አንድ ሰውም በፊቱ ያርዳታል።
4 ፤ ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል።
5 ፤ ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል።
6 ፤ ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል።
7 ፤ ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል።
8 ፤ ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።
9 ፤ ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ያከማቻል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኵሰትም ለሚያነጻ ውኃ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው።
10 ፤ የጊደሪቱንም አመድ ያከማቸ ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል።
11 ፤ የሞተውን ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል፤
12 ፤ በዚህም ውኃ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ያጠራል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያጠራ ንጹሕ አይሆንም።
13 ፤ የሞተውን ሰው በድን የነካ ሁለመናውን ባያጠራ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኵሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው።
14 ፤ ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል።
15 ፤ መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው።
16 ፤ በሜዳም በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን አጥንት ወይም መቃብር የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል።
17 ፤ ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለርኩሱ ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይቀላቀልበታል።
18 ፤ ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ያጠልቀዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ አጥንቱንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ላይ ይረጨዋል፤
19 ፤ ንጹሑም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን በርኩሱ ላይ ይረጨዋል፤ ባሰባተኛውም ቀን ያጠራዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በማታም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል።
20 ፤ ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባያጠራ፥ ያ ሰው የእግዚአብሔርን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ በሚያነጻ ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው።
21 ፤ ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሆንላችኋል፤ የሚያነጻውን ውኃ የሚረጭ ሰው ልብሱን ያጥባል፤ የሚያነጻውንም ውኃ የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
22 ፤ ርኩሱም የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።