ኦሪት ዘኍልቍ
ምዕራፍ 4
እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2 ፤ ከሌዊ ልጆች መካከል በየወገናቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች የቀዓትን ልጆች ድምር ውሰድ፤
3 ፤ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ በመገናኛው ድንኳን ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡበትን ሁሉ ትደምራለህ።
4 ፤ በመገናኛው ድንኳን በንዋየ ቅድሳቱ ዘንድ የቀዓት ልጆች ሥራ ይህ ነው፤
5 ፤ ከሰፈሩ በተነሡ ጊዜ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚሸፍነውን መጋረጃ ያውርዱ፥ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤
6 ፤ በላዩም የአቆስጣውን ቁርበት መሸፈኛ ያድርጉበት፥ ከእርሱም በላይ ሁለንተናው ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
7 ፤ በገጽ ኅብስት ገበታ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ በእርሱም ላይ ወጭቶቹን፥ ጭልፋዎቹንም፥ ጽዋዎቹንም፥ ለማፍሰስም መቅጃዎቹን ያድርጉ፤ ሁልጊዜም የሚኖር እንጀራ በእርሱ ላይ ይሁን።
8 ፤ በእነርሱም ላይ ቀይ መጐናጸፊያ ይዘርጉ፥ በአቆስጣውም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
9 ፤ ሰማያዊውንም መጐናጸፊያ ይውሰዱ፥ የሚያበራውንም መቅረዝ፥ ቀንዲሎቹንም፥ መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም፥ እርሱንም ለማገልገል የዘይቱን ዕቃዎች ሁሉ ይሸፍኑ፤
10 ፤ እርሱንና ዕቃዎቹን ሁሉ በአቆስጣ ቁርበት መሸፈኛ ውስጥ ያድርጉ፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት።
11 ፤ በወርቁም መሠዊያ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
12 ፤ በመቅደስም ውስጥ የሚያገልግሉበትን የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ ይውሰዱ፥ በሰማያዊውም መጐናጸፊያ ውስጥ ያስቀምጡት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት።
13 ፤ አመዱንም ከመሠዊያው ላይ ያስወግዱ፥ ሐምራዊውንም መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤
14 ፤ የሚያገለግሉበትን ዕቃውን ሁሉም ማንደጃዎቹን ሜንጦቹንም መጫሪያዎቹንም ድስቶቹንም፥ የመሠዊያውን ዕቃ ሁሉ ያስቀምጡበት፤ በእርሱም የአቆስጣን ቁርበት መሸፈኛ ይዘርጉ፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።
15 ፤ ከሰፈሩም ሲነሡ፥ አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና የመቅደሱን ዕቃ ሁሉ ከሸፈኑ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ የቀዓት ልጆች ሊሸከሙት ይመጣሉ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን አይንኩ። በመገናኛው ድንኳን ዘንድ የቀዓት ልጆች ሸክም ይህ ነው።
16 ፤ የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት በጣፋጩም ዕጣን ላይ፥ ሁልጊዜም በሚቀርበው በእህሉ ቍርባንና በቅባቱ ዘይት ላይ ይሾም፤ ማደሪያውን ሁሉ፥ በእርሱም ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ መቅደሱንና ዕቃውን ይጠብቃል።
17 ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
18 ፤ የቀዓትን ወገኖች ነገድ ከሌዋውያን መካከል አታጥፉአቸው፤
19 ፤ ነገር ግን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በቀረቡ ጊዜ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እንጂ እንዳይሞቱ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ይግቡ፥ ለሰውም ሁሉ ሥራውንና ሸክሙን ይዘዙ፤
20 ፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ ንዋየ ቅድሳቱን ለድንገት እንኳ ለማየት አይግቡ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
22 ፤ የጌድሶንን ልጆች ድምር ደግሞ በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገኖቻቸውም ውሰድ።
23 ፤ የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው።
24 ፤ የጌድሶናውያን ወገኖች ሥራ በማገልገልና በመሸከም ይህ ነው፤
25 ፤ የማደሪያውን መጋረጆች፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መደረቢያውን፥ በላዩም ያለውን የአቆስጣውን ቁርበት መደረቢያ፥ የመገናኛውንም ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥
26 ፤ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለውን የአደባባዩን መጋረጃ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቻቸውንም፥ ለማገልገልም የሚሠሩበትን ዕቃ ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህ ያገልግሉ።
27 ፤ የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፥ ሸክማቸውም ሁሉ፥ ሥራቸውም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ ትእዛዝ ይሁን፤ የሚደርስባቸውንም ሸክም ሁሉ ትነግሩአቸዋላችሁ።
28 ፤ የጌድሶናውያን ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ይህ ነው፤ ከካህኑ ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ይሆናሉ።
29 ፤ የሜራሪንም ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቍጠራቸው።
30 ፤ የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው።
31 ፤ በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ባለው አገልግሎታቸው ሁሉ፥ የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎቹም፥ ተራዳዎቹም፥ እግሮቹም፥
32 ፤ በዙሪያውም የሚቆሙት የአደባባዩ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም፥ ዕቃዎቹና ማገልገያዎቹ ሸክማቸው ነው፤ የሚጠብቁትንም የሸክማቸውን ዕቃ ሁሉ በስማቸው ቍጠሩ።
33 ፤ የሜራሪ ልጆች ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ከካህኑ ክአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች በየአገልግሎታቸው ሁሉ ይህ ነው።
34 ፤ ሙሴና አሮንም የሕቡም አለቆች የቀዓትን ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቈጠሩአቸው።
35 ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ወደ አገግሎት የገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቈጠሩአቸው፤
36 ፤ በየወገናቸውም ከእነርሱ የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ነበሩ።
37 ፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከቀዓታውያን ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።
38 ፤ በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት የጌድሶን ልጆች፥
39 ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የገቡት፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥
40 ፤ በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ።
41 ፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከጌድሶን ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።
42 ፤ በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥
43 ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወደ አገልግሎት የገቡት ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥
44 ፤ በየወገናቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
45 ፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።
46 ፤ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች ከሌዋውያን የተቈጠሩት ሁሉ፥ ሙሴና አሮን የእስራኤልም አለቆች የቈጠሩአቸው፥
47 ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራውን ለመሥራትና ዕቃውን ለመሸከም የገቡት ሁሉ፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥
48 ፤ ከእነርሱ የተቈጠሩት ስምንት ሺህ እምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ።
49 ፤ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ እያንዳንዳቸው በየአገልግሎታቸውና በየሸክማቸው በሙሴ እጅ ተቈጠሩ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በእርሱ ተቈጠሩ።