ምዕራፍ 31

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ስለ እስራኤል ልጆች በቀል ምድያማውያንን ተበቀል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ።
3 ፤ ሙሴም ሕዝቡን። ከእናንተ መካከል ሰዎች ለጦርነት ይሰለፉ፤ ስለ እግዚአብሔር በቀል ምድያምን ይበቀሉ ዘንድ በምድያም ላይ ይሂዱ፤
4 ፤ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ከየነገዱ አንድ ሺህ ሰው ወደ ጦርነት ስደዱ ብሎ ተናገራቸው።
5 ፤ ከእስራኤልም አእላፋት አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ፥ ለጦርነት የተሰለፉ ሰዎች ተሰጡ።
6 ፤ ሙሴም ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ ወደ ጦርነት ሰደደ፤ እነርሱንና የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ወደ ጦርነት ሰደዳቸው፤ የመቅደሱንም ዕቃ የሚነፋውንም መለከት በእጁ ሰጠው።
7 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ከምድያም ጋር ተዋጉ፥ ወንዶችንም ሁሉ ገደሉ።
8 ፤ ከተገደሉትም ጋር የምድያምን ነገሥታት ገደሉአቸው፤ አምስቱም የምድያም ነገሥታት ኤዊ፥ ሮቆም፥ ሱር፥ ሑር፥ ሪባ ነበሩ፤ የቢዖርንም ልጅ በለዓምን ደግሞ በሰይፍ ገደሉት።
9 ፤ የእስራኤልም ልጆች የምድያምን ሴቶችና ልጆቻቸውን ማረኩ፤ እንስሶቻቸውንና መንጎቻቸውንም ዕቃቸውንም ሁሉ በዘበዙ።
10 ፤ የተቀመጡባቸውን ከተሞቻቸውን ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም ሁሉ በእሳት አቃጠሉ።
11 ፤ የሰውንና የእንስሳን ምርኮና ብዝበዛ ሁሉ ወሰዱ።
12 ፤ የማረኩአቸውንም ሰዎች ምርኮውንና ብዝበዛውን ወደ ሙሴና ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር፥ በዮርዳኖስም አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ወዳለው ሰፈር አመጡ።
13 ፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ሊገናኙአቸው ወጡ።
14 ፤ ሙሴም ከዘመቻ በተመለሱት በጭፍራ አለቆች፥ በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ።
15 ፤ ሙሴም አላቸው። በውኑ ሴቶችን ሁሉ አዳናችኋቸውን?
16 ፤ እነሆ፥ እነዚህ በፌጎር ምክንያት በበለዓም ምክር እግዚአብሔርን ይበድሉ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ዕንቅፋት ሆኑ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሠፍት ሆነ።
17 ፤ አሁን እንግዲህ ከልጆቹ ወንዱን ሁሉ ግደሉ፥ ወንድንም በመኝታ የሚያውቁትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ።
18 ፤ ወንድን የማያውቁትን ሴቶች ልጆችን ሁሉ ግን ለራሳችሁ አድኑአቸው።
19 ፤ ከሰፈሩም ውጭ ሰባት ቀን ስፈሩ፤ ሰውን የገደለ ሁሉ የተገደለውንም የዳሰሰ ሁሉ፥ እናንተ የማረካችኋቸውም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጉ።
20 ፤ ልብስንም፥ ከቁርበትም የተዘጋጀውን ሁሉ፥ ከፍየልም ጠጕር ከእንጨትም የተሠራውን ሁሉ ንጹሕ አድርጉ።
21 ፤ ካህኑም አልዓዛር ከሰልፍ የመጡትን ሰዎች አላቸው። እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው የሕጉ ሥርዓት ይህ ነው፤
22 ፤ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንም፥ ብረቱንም፥ ቆርቆሮውንም፥
23 ፤ አረሩንም፥ በእሳት ለማለፍ የሚችለውን ሁሉ በእሳት ታሳልፉታላችሁ፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በማንጻት ውኃ ደግሞ ይጠራል። በእሳትም ለማለፍ የማይችለውን በውኃ ታሳልፉታላችሁ።
24 ፤ በሰባተኛውም ቀን ልብሳችሁን እጠቡ፥ ንጹሕም ትሆናላችሁ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትቀርባላችሁ።
25 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
26 ፤ አንተና ካህኑ አልዓዛር የማኅበሩም አባቶች አለቆች የተማረኩትን ሰውና እንስሳ ቍጠሩ።
27 ፤ ምርኮውንም በተዋጉትና ወደ ሰፍል በወጡት፥ በማኅበሩም ሁሉ መካከል አስተካክለህ ክፈል።
28 ፤ ከእነዚያም ከተዋጉት ወደ ሰልፍም ከወጡት ሰልፈኞች ዘንድ፥ ከሰዎችም ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከአምስት መቶ አንድ ለእግዚአብሔር ግብር አውጣ።
29 ፤ ከድርሻቸው ወስደህ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ለካህኑ ለአልዓዛር ስጠው።
30 ፤ ከእስራኤልም ልጆች ድርሻ ከሰዎች ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከከብቶችም ሁሉ ከአምሳ አንድ ትወስዳለህ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ለሌዋውያን ትሰጣለህ።
31 ፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።
32 ፤ ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎችም ከወሰዱት ብዝበዛ ያስቀሩት ምርኮ እንዲህ ሆነ፤ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ በጎች፥
33
34 ፤ ሰባ ሁለት ሺህ በሬዎች፥ ስድሳ አንድ ሺህ አህዮች፥
35 ፤ ወንድ ከማያውቁ ሴቶችም ሠላሳ ሁለት ሺህ ነፍስ።
36 ፤ በዘመቻም ለነበሩ ሰዎች ድርሻ የሆነ እኵሌታ ከበግ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች ነበረ፥
37 ፤ ከበጎችም የእግዚአብሔር ግብር ስድስት መቶ ሰባ አምስት ነበረ።
38 ፤ በሬዎችም ሠላሳ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሰባ ሁለት ነበረ።
39 ፤ አህዮቹም ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ስድሳ አንድ ነበረ።
40 ፤ ሰዎቹም አሥራ ስድስት ሺህ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሠላሳ ሁለት ነበረ።
41 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን የሆነውን ግብር ለካህኑ ለአልዓዛር ሰጠው።
42 ፤ ከእስራኤል ልጆች እኩሌታም፥ ወደ ሰልፍ ከወጡት ወንዶች ላይ ሙሴ የለየው፥
43 ፤ የማኅበሩ ድርሻ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች፥
44 ፤ ሠላሳ ስድስት ሺህ በሬዎች፥
45 ፤ ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ አህዮች፥
46 ፤ አሥራ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ።
47 ፤ ከእስራኤል ልጆች ድርሻ ሙሴ ከሰውና ከእንስሳ ከአምሳ አንድ ወሰደ፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጠ።
48 ፤ በሠራዊት አእላፋት ላይ የተሾሙት አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች፥ ወደ ሙሴ ቀረቡ፥
49 ፤ ሙሴንም። እኛ ባሪያዎችህ ወደ ሰልፍ የወጡትን ከእጃችን በታች ያሉትን ቈጠርን፥ ከእኛም አንድ አልጐደለም።
50 ፤ ሰውም ሁሉ ካገኘው ከወርቅ ዕቃ፥ ከእግር አልቦም፥ ከአምባርም፥ ከቀለበትም፥ ከጕትቻም፥ ከድሪውም ለነፍሳችን በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይልን ዘንድ ለእግዚአብሔር መባ አምጥተናል አሉት።
51 ፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁንና በልዩ ልዩ የተሠራውን ዕቃ ሁሉ ከእጃቸው ተቀበሉ።
52 ፤ ሻለቆችም የመቶ አለቆችም ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ያቀረቡት ወርቅ ሁሉ አሥራ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ሰቅል ነበረ።
53 ፤ ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ሁሉ ከምርኮአቸው ለራሳቸው ወሰዱ።
54 ፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁን ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ወስደው በእግዚአብሔር ፊት ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ወደ መገናኛው ድንኳን አገቡት።