ምዕራፍ 46

ስለ አሕዛብ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2 ስለ ግብጽ፤ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በከርከሚሽ ስለ ነበረው፥ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታው ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ኒካዑ ሠራዊት።
3 ጋሻ ጦር አዘጋጁ ወደ ሰልፍም ቅረቡ።
4 ፈረሰኞች ሆይ፥ ፈረሶችን ለጕሙና ውጡ፥ ራስ ቍርንም ደፍታችሁ ቁሙ፤ ጦርንም ሰንግሉ ጥሩርንም ልበሱ።
5 ፈርተው ወደ ኋላ ሲመለሱ፥ ኃያላኖቻቸውም ሲደበደቡ ወደ ኋላቸውም ሳይመለከቱ ፈጥነው ሲሸሹ ለምን አየሁ? በዚህና በዚያ ድንጋጤ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር።
6 ፈጣኑ አያመልጥም ኃያሉም አይድንም፤ በሰሜን በኤፍራጥስ ወንዝ በኩል ተሰናክለው ወደቁ።
7 ይህ እንደ ግብጽ ወንዝ የሚነሣ፥ ውኃውም እንደ ወንዝ የሚናወጥ ማን ነው?
8 ግብጽ እንደ ግብጽ ወንዝ ይነሳል ውኃውም እንደ ወንዙ ይናወጣል፤ እርሱም።እነሣለሁ ምድርንም ሁሉ እከድናለሁ፤ ከተሞችንና የሚኖሩባቸውን አጠፋለሁ ብሎአል።
9 ፈረሶች ሆይ፥ ውጡ፤ ሰረገሎችም ሆይ፥ ንጐዱ፤ ጋሻም የሚያነግቡ የኢትዮጵያና የፋጥ ኃያላን፥ ቀስትንም ይዘው የሚስቡ የሉድ ኃያላን ይውጡ።
10 ያ ቀን ጠላቶቹን የሚበቀልበት የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የበቀል ቀን ነው፤ ሰይፍ በልቶ ይጠግባል በደማቸውም ይሰክራል፥ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ መሥዋዕት አለውና።
11 ድንግሊቱ የግብጽ ልጅ ሆይ፥ ወደ ገለዓድ ውጪ የሚቀባንም መድኃኒት ውሰጂ፤ መድኃኒትን ያበዛሽው በከንቱ ነው፤ መዳን የለሽም።
12 ኃያሉ በኃያሉ ላይ ተሰናክሎ ሁለቱ በአንድነት ወድቀዋልና አሕዛብ ጕስቍልናሽን ሰምተዋል፥ ልቅሶሽም ምድርን ሞልቶአታል።
13 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እንዲመጣና የግብጽን ምድር እንዲመታ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
14 በግብጽ ተናገሩ፥ በሚግዶልም አሰሙ፥ በሜምፎስና በጣፍናስ አሰሙ፤ ሰይፍ በዙሪያህ ያለውን በልቶአልና። ተነሥ ተዘጋጅም በሉ።
15 ኃይለኞችህ ስለ ምን ተወገዱ? እግዚአብሔር ስላደከማቸው አልቆሙም።
16 ብዛታቸውም ተሰናከለ፥ ሰውም አንዱ በአንዱ ላይ ወደቀ፤ እነርሱም። ተነሡ፥ ከሚያስጨንቅ ሰይፍ ፊት ወደ ወገናችን ወደ ተወለድንባት ምድር እንመለስ አሉ።
17 በዚያም የግብሥ ንጉሥ ፈርዖንን፦ ሰዓቱን የሚያሳልፍ ጕረኛ ብለው ጠሩት።
18 እኔ ሕያው ነኝና በተራሮች መካከል እንዳለ እንደ ታቦር፥ በባሕርም አጠገብ እንዳለ እንደ ቀርሜሎስ፥ እንዲሁ በእውነት ይመጣል፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ።
19 አንቺ በግብጽ የምትቀመጪ ልጅ ሆይ፥ ሜምፎስ ባድማ ትሆናለችና፥ ትቃጠልማለችና፥ የሚቀመጥባትም አይገኝምና ለምርኮ የሚሆን ዕቃ አዘጋጂ።
20 ግብጽ የተዋበች ጊደር ናት፤ ጥፋት ግን ይመጣል፥ ከሰሜን በኩል ይመጣባታል።
21 በእርስዋም ያሉ የተቀጠሩ ሠራተኞች እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፤ የጥፋታቸው ቀንና የመጐብኘታቸው ጊዜ መጥቶባቸዋልና ተመለሱ፥ በአንድነትም ሸሹ፥ አልቆሙምም።
22 ከሠራዊትም ጋር ይሄዳሉና ድምፅ እንደ እባብ ይተምማል፤ እንደ እንጨት ቈራጮችም በምሳር ይመጡባታል።
23 ይቈጠሩ ዘንድ የማይቻሉትን የዱርዋን ዛፎች ይቈርጣሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከአንበጣ ይልቅ በዝተዋልና ቍጥርም የላቸውምና።
24 የግብጽ ልጅ ታፍራለች፤ በሰሜን ሕዝብ እጅ አልፋ ትሰጣለች።
25 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የኖእ አሞንን፥ ፈርዖንንም፥ ግብጽንም፥ አማልክቶችዋንና ነገሥታቶችዋንም፥ ፈርዖንና በእርሱም የሚታመኑትን እቀጣለሁ፤
26 ነፍሳቸውንም በሚፈልጉ ሰዎች እጅ፥ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡክደነፆር እጅ፥ በባሪያዎቹም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ አንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች፥ ይላል እግዚአብሔር።
27 ነገር ግን አንተ ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ አትደንግጥ፤ እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከተማረከባት ምድር አድናለሁ፤ ያዕቆብም ተመልሶ ያርፋል ተዘልሎም ይቀመጣል፥ ማንም አያስፈራውምም።
28 አንተ ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አንተንም ያሰደድሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁና፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ በመጠን እቀጣሃለሁ፥ ያለ ቅጣትም አልተውህም።