ምዕራፍ 35

በይሁዳ ንጉስ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው።
2 ወደ ሬካባውያን ቤት ሄደህ ተናገራቸው፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ከጓዳዎቹ ወደ አንዲቱ አግባቸው የወይን ጠጅም አጠጣቸው።
3 የከባስንን ልጅ የኤርምያስን ልጅ ያእዛንያን ወንድሞቹንም ልጆቹንም ሁሉ የሬካባውያንን ወገን ሁሉ ወሰድኋቸው፤
4 ወደ እግዚአብሔርም ቤት በበረኛው በሰሎም ልጅ በመዕሤያ ጓዳ በላይ ባለው በአለቆች ጓዳ አጠገብ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ጌዴልያ ልጅ ወደ ሐናን ልጆች ጓዳ አገባኋቸው።
5 በሬካባውያንም ልጆች ፊት የወይን ጠጅ የሞላባቸውን ማድጋዎችንና ጽዋዎችን አኑሬ። የወይኑን ጠጅ ጠጡ አልኋቸው።
6 እነርሱ ግን እንዲህ አሉ። የወይኑን ጠጅ አንጠጣም፥ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ እንዲህ ብሎ አዝዞናልና። እናንተና ልጆቻችሁ ለዘላለም የወይን ጠጅ አትጠጡ።
7 በምትኖሩባት ምድር ላይ ብዙ ዘመን እንድትኖሩ፥ በዕድሜአችሁ ሙሉ በድንኳን ውስጥ ተቀመጡ እንጂ ቤትን አትሥሩ፥ ዘርንም አትዝሩ፥ ወይንም አትትከሉ፥ አንዳችም አይሁንላችሁ።
8 እኛም የአባታችንን የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብን ቃል ባዘዘን ነገር ሁሉ ታዝዘናል፤ እኛም ሚስቶቻችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ዕድሜአችንን ሙሉ የወይን ጠጅ አልጠጣንም፤
9 የምንቀመጥበትንም ቤት አልሠራንም፤ የወይን ቦታና እርሻ ዘርም የለንም፤
10 በድንኳንም ውስጥ ተቀምጠናል፥ ታዝዘናል፥ አባታችንም ኢዮናዳብ ያዘዘንን ሁሉ አድርገናል።
11 ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደዚህች ምድር በመጣ ጊዜ። ኑ ከከለዳውያን ሠራዊትና ከሶርያ ሠራዊት ፊት የተነሣ ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ አልን፤ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ተቀመጥን።
12 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ።
13 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሂድና ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ተናገር እንዲህም በላቸው። ቃሌን ትሰሙ ዘንድ ተግሣጽን አትቀበሉምን? ይላል እግዚአብሔር።
14 የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ልጆቹ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ ያዘዛቸው ቃል ተፈጸመ፤ ለአባታቸውም ትእዛዝ ታዝዘዋልና እስከ ዛሬ ድረስ አይጠጡም፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ተናግሬአችኋለሁ፤ ተናገርሁ፥ ሆኖም አልሰማችሁኝም።
15 ደግሞም። እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ ሥራችሁንም አሳምሩ፥ ታመልኩአቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠሁት ምድር ትቀመጣላችሁ እያልሁ በማለዳ ተነሥቼ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ጆሬአችሁን አላዘነበላችሁም እኔንም አልሰማችሁኝም።
16 የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ልጆች አባታቸው ያዘዛቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋልና፥ ይህ ሕዝብ ግን አልሰማኝምና፤
17 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በተናገርኋቸው ጊዜ አልሰሙምና፥ በጠራኋቸውም ጊዜ አልመለሱልኝምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በሚቀመጡ ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ።
18 ኤርምያስም ሬካባውያንን እንዲህ አላቸው። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለአባታችሁ ለኢዮናዳብ ትእዛዝ ታዝዛችኋልና፥ ትእዛዙንም ሁሉ ጠብቃችኋልና፥ ያዘዛችሁንም ፈጽማችኋልና፤
19 ስለዚህ በፊቴ የሚቆም ሰው ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን ለዘላለም አይታጣም።