ትንቢተ ኤርምያስ
ምዕራፍ 37
የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ያነገሠው የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ፋንታ ነገሠ።
2 እርሱም ሆነ ባሪያዎቹ የአገሩም ሕዝብ በነቢዩ በኤርምያስ እጅ የተናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።
3 ንጉሡም ሴዴቅያስ። ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ጸልይ ብሎ የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ።
4 እርሱንም በግዞት ቤት ገና አላገቡትም ነበርና ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ይወጣና ይገባ ነበር።
5 የፈርዖንም ሠራዊት ከግብጽ ወጣ፤ ኢየሩሳሌምንም ከብበዋት የነበሩ ከለዳውያን ይህን ወሬ በሰሙ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ተመለሱ።
6 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ።
7 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከእኔ ትጠይቁ ዘንድ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት። እነሆ፥ ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሠራዊት ወደ አገሩ ወደ ግብጽ ይመለሳል።
8 ከለዳውያንም ተመልሰው ይህችን ከተማ ይዋጉአታል ይይዙአትማል በእሳትም ያቃጥሉአታል።
9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አይሄዱምና። ከለዳውያን በእርግጥ ከእኛ ዘንድ ይሄዳሉ ብላችሁ ራሳችሁን አታታልሉ።
10 እናንተም የሚዋጉትን የከለዳውያንን ሠራዊት ሁሉ ብትመቱት ኖሮ፥ ከእነርሱም የተወጉት ብቻ ቢቀሩ ኖሮ፥ ሁሉ እያንዳንዱ በድንኳኑ ተነሥቶ ይህችን ከተማ በእሳት ባቃጠሉአት ነበር።
11 የከለዳውያንም ሠራዊት ከፈርዖን ሠራዊት ፊት የተነሣ ከኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ፥
12 ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል የርስቱን እድል ፈንታ ከዚያ ይቀበል ዘንድ ወደ ብንያም አገር ሊሄድ ከኢየሩሳሌም ወጣ።
13 በብንያምም በር በነበረ ጊዜ የሐናንያ ልጅ የሰሌምያ ልጅ የሪያ የተባለ የዘበኞች አለቃ በዚያ ነበረ፤ እርሱም። ወደ ከለዳውያን መኰብለልህ ነው ብሎ ነቢዩን ኤርምያስን ያዘው።
14 ኤርምያስም። ሐሰት ነው፤ ወደ ከለዳውያን መኰብለሌ አይደለም አለ፤ እርሱ ግን አልሰማውም፥ የሪያም ኤርምያስን ይዞ ወደ አለቆች አመጣው።
15 አለቆችም ተቈጥተው ኤርምያስን መቱት፥ የጸሐፊውንም የዮናታንን ቤት የግዞት ቤት አድርገውት ነበርና በዚያ አኖሩት።
16 ኤርምያስም ወደ ጕድጓድ ቤት ወደ ጓዳዎቹ ገባ፤ ኤርምያስም በዚያ ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ፥
17 ንጉሡ ሴዴቅያስ ልኮ አስመጣው፥ ንጉሡም በቤቱ። በውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ቃል አለን? ብሎ በቈይታ ጠየቀው። ኤርምያስም። አዎን አለ። ደግሞም። በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፈህ ትሰጣለህ አለ።
18 ኤርምያስም ደግሞ ንጉሡን ሴዴቅያስን እንዲህ አለው። በግዞት ቤት የጣላችሁኝ አንተን ወይስ ባሪያዎችህን ወይስ ሕዝብህን ምን በድያችሁ ነው?
19 የባቢሎን ንጉሥ በእናንተና በዚህች አገር አይመጣባችሁም ብለው ትንቢት ይናገሩላችሁ የነበሩ ነቢያቶቻችሁ ወዴት አሉ?
20 ንጉሡ ጌታዬ ሆይ፥ እንድትሰማኝ አሁን እለምንሃለሁ፤ እባክህ፥ ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በዚያ እንዳልሞት ወደ ጸሐፊው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ።
21 ንጉሡም ሴዴቅያስ አዘዘ፥ ኤርምያስንም በግዞት ቤት አደባባይ አኖሩት፥ እንጀራም ሁሉ ከከተማ እስኪጠፋ ድረስ ዕለት ዕለት አንድ አንድ እንጀራ ከጋጋሪዎች መንገድ ይሰጡት ነበር። እንዲሁም ኤርምያስ በግዞት ቤት አደባባይ ተቀምጦ ነበር።