ምዕራፍ 42

የጭፍራ አለቆችም ሁሉ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የሆሻያም ልጅ ያእዛንያ ሕዝብም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ቀረቡ፥
2 -
3 ነብዩንም ኤርምያስን። ዓይኖችህ እንዳዩን ከብዙ ጥቂት ቀርተናልና ልመናችን፥ እባክህ፥ በፊትህ ትድረስ፤ አምላክህም እግዚአብሔር የምንሄድበትን መንገድና የምናደርገውን ነገር ያሳየን ዘንድ ስለ እኛ፥ ስለዚህ ቅሬታ ሁሉ፥ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት።
4 ነቢዩም ኤርምያስ። ሰምቻችኋለሁ፤ እነሆ፥ እንደ ቃላችሁ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ እግዚአብሔርም የሚመልስላችሁን ሁሉ እነግራችኋለሁ፥ ከእናንተም ምንም አልሸሽግም አላቸው።
5 ኤርምያስንም። አምላክህ እግዚአብሔር በአንተ እጅ ወደ እኛ የላከውን ነገር ሁሉ ባናደርግ፥ እግዚአብሔር በመካከላችን እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁን።
6 የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል በመስማታችን መልካም እንዲሆንልን፥ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን፥ አንተን ወደ እርሱ የምንልክህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን አሉት።
7 ከአሥር ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ።
8 የቃሬያንም ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆች ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡንም ሁሉ ጠራ፥ እንዲህም አላቸው።
9 ጸሎታችሁን በፊቱ አቀርብ ዘንድ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
10 ስላደረግሁባችሁ ክፉ ነገር ተጸጽቻለሁና በዚህች ምድር ብትቀመጡ እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም።
11 ከምትፈሩት ከባቢሎን ንጉሥ አትፍሩ፤ አድናችሁ ዘንድ ከእጁም አስጥላችሁ ዘንድ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ፥ ይላል እግዚአብሔር።
12 እርሱ እንዲምራችሁ ወደ አገራችሁም እንዲመልሳችሁ እኔ እምራችኋለሁ።
13 እናንተ ግን። በዚህች ምድር አንቀመጥም ብትሉ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥
14 እናንተም። አይደለም፤ ሰልፍ ወደማናይባት የመለከትም ድምፅ ወደማንሰማባት ወደማንራብባትም ወደ ግብጽ ምድር እንሄዳለን በዚያም እንቀመጣለን ብትሉ፥
15 እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፥ አሁን እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ግብጽ ትገቡ ዘንድ በዚያም ትቀመጡ ዘንድ ፊታችሁን ብታቀኑ፥
16 የምትፈሩት ሰይፍ በዚያ በግብጽ ምድር ያገኛችኋል፥ ስለ እርሱም የምትደነግጡበት ራብ በዚያ በግብጽ ይደርስባቸኋል፥ በዚያም ትሞታላችሁ።
17 ወደ ግብጽም ይገቡ ዘንድ በዚያም ይቀመጡ ዘንድ ፊታቸውን በሚያቀኑ ሰዎች ሁሉ እንዲህ ይሆንባቸዋል፤ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታሉ፤ እኔም ከማመጣባቸው ክፉ ነገር ማንም አይቀርም፥ ማንም አያመልጥም።
18 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ቍጣዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ላይ እንደ ፈሰሰ፥ እንዲሁ ወደ ግብጽ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ ይፈስስባችኋል፤ እናንተም ለጥላቻና ለመደነቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ትሆናላችሁ፥ ይህንም ስፍራ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩትም።
19 እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፥ እግዚአብሔር። ወደ ግብጽ አትግቡ ብሎ ተናግሮባችኋልና ዛሬ እንዳስጠነቀቅኋችሁ በእርግጥ እወቁ።
20 እናንተ። ስለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፥ አምላካችንም እግዚአብሔር የሚናገርህን ሁሉ ንገረን እኛም እናደርገዋለን ብላችሁ ወደ እግዚአብሔር ወደ አምላካችሁ ልካችሁኝ ነበርና ራሳችሁን አታልላችኋል።
21 እኔም ዛሬ ነግሬአችኋለሁ፥ ወደ እናንተም በላከኝ ነገር ሁሉ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁም።
22 አሁንም ሄዳችሁ እንድትቀመጡ በወደዳችሁበት ስፍራ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እንድትሞቱ በእርግጥ እወቁ።