ምዕራፍ 24

የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን የይሁዳንም አለቆች ጠራቢዎችንና ብረት ሠራተኞችን ከኢየሩሳሌም ማርኮ ወደ ባቢሎን ካፈለሳቸው በኋላ፥ እግዚአብሔር አሳየኝ፥ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መቅደስ ፊት ሁለት ቅርጫት በለስ ተቀምጠው ነበር።
2 በአንደኛይቱ ቅርጫት አስቀድሞ እንደ ደረሰ በለስ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረባት፤ በሁለተኛይቱ ቅርጫት ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ በለስ ነበረባት።
3 እግዚአብሔርም። ኤርምያስ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። በለስን አያለሁ፤ እጅግ መልካም የሆነ መልካም በለስ፥ ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ የሆነ ክፉ በለስ ነው አልሁ።
4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
5 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፥ እንዲሁ ከዚህ ስፍራ ወደ ከለዳውያን ምድር የሰደድሁትን የይሁዳን ምርኮ ለበጐነት እመለከተዋለሁ።
6 ዓይኔንም ለበጐነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም።
7 እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹምም ልባቸው ወደ እኔ ይመለሳሉና ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
8 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉው በለስ፥ እንዲሁ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን አለቆቹንም በዚህችም አገር የሚቀሩትን የኢየሩሳሌም ቅሬታ በግብጽም አገር የሚቀመጡትን እጥላቸዋለሁ።
9 በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ ለማላገጫና ለእርግማን ይሆኑ ዘንድ በምድር መንግሥታት ሁሉ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
10 ለእነርሱና ለአባቶቻቸውም ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እሰድዳለሁ።