ትንቢተ ኤርምያስ
ምዕራፍ 15
እግዚአብሔርም እንደዚህ አለኝ። ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም፥ ልቤ ወደዚህ ሕዝብ አይዘነብልም፤ ከፊቴ ጣላቸው፤ ይውጡ።
2 እነርሱም። ወዴት እንውጣ ቢሉህ፥ አንተ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለሞት የሆነ ወደ ሞት፥ ለሰይፍም የሆነ ወደ ሰይፍ፥ ለራብም የሆነ ወደ ራብ፥ ለምርኮም የሆነ ወደ ምርኮ ትላቸዋለህ።
3 ሰይፍን ለመግደል ውሾችንም ለመጐተት የሰማያትንም ወፎች የምድርንም አራዊት ለመብላትና ለማጥፋት፥ አራቱን ዓይነት ጥፋት አዝዝባቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
4 የይሁዳም ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ስላደረገው ሁሉ በምድር መንግሥታት ሁሉ መካከል ለመከራ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
5 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ የሚራራልሽ ማን ነው? የሚያዝንልሽስ ማን ነው? ወይስ ስለ ደኅንነትሽ ይጠይቅ ዘንድ ፈቀቅ የሚል ማነ ነው?
6 አንቺ እኔን ጥለሻል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ወደ ኋላሽም ተመልሰሻል፤ ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቼ አጥፍቼሻለሁ፤ ከይቅርታ ደክሜአለሁ።
7 በአገርም ደጆች ውስጥ በመንሽ አበጥሬአቸዋለሁ፤ የወላድ መካን አድርጌአቸዋለሁ፥ ሕዝቤንም አጥፍቼአለሁ፤ ከመንገዳቸውም አልተመለሱም።
8 መበለቶቻቸውም ከባሕር አሸዋ ይልቅ በዝተውብኛል፤ በብላቴኖች እናት ላይ በቀትር ጊዜ አጥፊውን አምጥቻለሁ፤ ጣርንና ድንጋጤን በድንገት አምጥቼባታለሁ።
9 ሰባት የወለደች ደክማለች፥ ነፍስዋንም አውጥታለች፤ ቀን ገና ሳለ ፀሐይዋ ገብታባታለች፤ አፍራለች ተዋርዳማለች፤ የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣለሁ።
10 እናቴ ሆይ፥ ወዮልኝ! ለምድር ሁሉ የክርክርና የጥል ሰው የሆንሁትን ወለድሽኝ ለማንም አላበደርሁም፥ ማንም ለእኔ አላበደረም፥ ነገር ግን ሁሉ ይረግመኛል።
11 እግዚአብሔር እንዲህ አለ። በእውነት ለደኅንነትህ አጸናሃለሁ፤ በእውነት በመከራና በጭንቅ ጊዜ ጠላትህ እንዲለምንህ አደርገዋለሁ።
12 በውኑ ብረትን፥ የሰሜንን ብረት፥ ናስንም የሚሰብር አለን?
13 በዳርቻህ ሁሉ ስላለ ኃጢአትህ ሁሉ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ለመበዝበዝ በከንቱ እሰጣለሁ።
14 የምታቃጥላችሁ እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና ከጠላቶችህ ጋር ወደማታውቀው ምድር አሳልፍሃለሁ።
15 አቤቱ፥ አንተ ታውቃለህ፤ አስበኝ ጐብኘኝም የሚያሳድዱኝንም ተበቀላቸው እንጂ አትታገሣቸው፤ ስለ አንተ ስድብን እንደ ታገሥሁ እወቅ።
16 ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ፤ አቤቱ፥ የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ።
17 በዋዘኞችና በደስተኞች ጉባኤ አልተቀመጥሁም፤ ቍጣን ሞልተህብኛልና በእጅህ ፊት ለብቻዬ ተቀመጥሁ።
18 ስለ ምን ሕመሜ አዘወተረኝ? ቍስሌስ ስለ ምን የማይፈወስ ሆነ? ስለ ምንስ። አልሽርም አለ? በውኑ እንደ ሐሰተኛ ምንጭ፥ እንዳልታመነች ውኃ ትሆነኛለህን?
19 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ብትመለስ እመልስሃለሁ በፊቴም ትቆማለህ፤ የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ፤ እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ፥ አንተ ግን ወደ እነርሱ አትመለስም።
20 ለዚህም ሕዝብ የተመሸገ የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፤ ይዋጉሃል እኔ ግን ለማዳን ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም።
21 ከክፉ ሰዎችም እጅ እታደግሃለሁ፥ ከጨካኞችም ጡጫ እቤዥሃለሁ።