ምዕራፍ 20

በእግዚአብሔርም ቤት የተሾመው አለቃ የካህኑ የኢሜር ልጅ ጳስኮር ኤርምያስ በዚህ ነገር ትንቢት ሲናገር ሰማ።
2 ጳስኮርም ነቢዩን ኤርምያስን መታው፥ በእግዚአብሔርም ቤት በነበረው በላይኛው በብንያም በር ባለው በእግር ግንድ ውስጥ አኖረው።
3 በነጋውም ጳስኮር ኤርምያስን ከግንድ ውስጥ አወጣው። ኤርምያስም እንዲህ አለው። እግዚአብሔር ስምህን። ማጎርሚሳቢብ እንጂ ጳስኮር ብሎ አይጠራህም።
4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ለራስህና ለወዳጆችህ ሁሉ ፍርሃት አደርግሃለሁ፤ እነርሱም በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ ዓይኖችህም ያያሉ፤ ይሁዳንም ሁሉ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል በሰይፍም ይገድላቸዋል።
5 የዚህችንም ከተማ ባለጠግነት ሁሉ ጥሪትዋንም ሁሉ ክብርዋንም ሁሉ የይሁዳንም ነገሥታት መዝገብ ሁሉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እነርሱም ይበዘብዙአቸዋል ይዘውም ወደ ባቢሎን ያፈልሱአቸዋል።
6 አንተም፥ ጳስኮር ሆይ፥ በቤትህም የሚኖሩት ሁሉ ተማርካችሁ ትሄዳላችሁ፤ አንተም በሐሰትም ትንቢት የተናገርህላቸው ወዳጆችህ ሁሉ ወደ ባቢሎን ትገባላችሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ፥ በዚያም ትቀበራላችሁ።
7 አቤቱ፥ አታለልኸኝ እኔም ተታለልሁ፥ ከእኔም በረታህ አሸነፍህም፤ ቀኑን ሁሉ መሳቂያ ሆኛለሁ፥ ሁሉም ያላግጡብኛል።
8 በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፤ ግፍና ጥፋት ብዬ እጮኻለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ቀኑን ሁሉ ስድብና ዋዛ ሆኖብኛልና።
9 እኔም። የእግዚአብሔርን ስም አላነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም ብል፥ በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፤ ደከምሁ፥ መሸከምም አልቻልሁም።
10 የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁ፥ ማስፈራራትም ከብቦኛል። መውደቄን የሚጠብቁ የሰላሜ ሰዎች ሁሉ። ምናልባት ይታለል እንደ ሆነ፥ እናሸንፈውም እንደ ሆነ፥ እርሱንም እንበቀል እንደ ሆነ፥ ክሰሱት እኛም እንከስሰዋለን ይላሉ።
11 እግዚአብሔር ግን እንደ ኃያልና እንደ ጨካኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ አያሸንፉም፤ አይከናወንላቸውምና በጽኑ እፍረት ያፍራሉ፥ ለዘላለምም በማይረሳ ጕስቍልና ይጐሰቍላሉ።
12 አቤቱ፥ ጻድቅን የምትመረምር ኵላሊትንና ልብን የምትመለከት የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ ክርክሬን ገልጬልሃለሁና በቀልህን በላያቸው ለይ።
13 ለእግዚአብሔር ዘምሩ እግዚአብሔርንም አመስግኑ፤ የችግረኛውን ነፍስ ከክፉ አድራጊዎች እጅ አድኖአልና።
14 የተወለድሁባት ቀን የተረገመች ትሁን፤ እናቴ እኔን የወለደችባት ቀን የተባረከች አትሁን።
15 ወንድ ልጅ ተወልዶልሃል ብሎ ለአባቴ የምሥራች ነግሮ ደስ ያሰኘው ሰው የተረገመ ይሁን።
16 ያም ሰው እግዚአብሔር ሳይጸጸት እንደ ገለበጣቸው ከተሞች ይሁን፥ በማለዳም ልቅሶን በቀትርም ጩኸትን ይስማ፤
17 እናቴ መቃብር ትሆነኝ ዘንድ ማኅፀንዋም ዘወትር ይዞኝ ያቆይ ዘንድ በማኅፀን ውስጥ አልገደለኝምና።
18 ድካምንና ጣርን አይ ዘንድ ዘመኔም በእፍረት ታልቅ ዘንድ ስለ ምን ከማኅፀን ወጣሁ?