ትንቢተ ኤርምያስ
ምዕራፍ 17
የይሁዳ ኃጢአት በብረት ብርዕና በተሾለ ዕብነ አልማዝ ተጽፎአል፤ በልባቸው ጽላትና በመሠዊያቸው ቀንዶች ተቀርጾአል።
2 ልጆቻቸውም ከለመለሙ ዛፎች በታችና በረዘሙት ኮረብቶች ላይ ያሉትን መሠዊያቸውንና የማምለኪያ ዐፀዳቸውን ያስባሉ።
3 በሜዳ ያለው ተራራዬ ሆይ፥ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችህም ስለ ኃጢአት በድንበሮችህ ሁሉ ለመበዝበዝ እሰጣለሁ።
4 አንተም የሰጠሁህን ርስት ትለቅቃለህ ለዘላለምም በማታውቃትም ምድር ለጠላቶቻችሁ ባሪያ አደርግሃለሁ፤ ለዘላለም የሚነድደውን እሳት በቍጣዬ አንድዳችኋልና።
5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው።
6 በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል።
7 በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።
8 በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።
9 የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?
10 እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ።
11 ያልወለደችውን እንደምታቅፍ ቆቅ፥ እንዲሁ በቅን ሳይሆን ባለጠግነትን የሚሰበስብ ሰው ነው፤ በእኩሌታ ዘመኑ ይተወዋል፥ በፍጻሜውም ሰነፍ ይሆናል።
12 የመቅደሳችን ስፍራ ከጥንት ጀምሮ ክፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው።
13 አቤቱ፥ የእስራኤል ተስፋ ሆይ፥ የሚተዉህ ሁሉ ያፍራሉ፤ ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ እግዚአብሔርን ትተዋልና በምድር ላይ ይጻፋሉ።
14 አቤቱ፥ ፈውሰኝ እኔም እፈወሳለሁ፤ አድነኝ እኔም እድናለሁ፤ አንተ ምስጋናዬ ነህና።
15 እነሆ። የእግዚአብሔር ቃል ወዴት አለች? አሁን ትምጣ ይሉኛል።
16 እኔም አንተን ተከትዬ እረኛ ከመሆን አልቸኰልሁም፥ የመከራንም ቀን አልወደድሁም፤ አንተ ታውቃለህ፤ ከከንፈሬ የወጣው በፊትህ ነበረ።
17 ለማስፈራራት አትሁንብኝ፤ በመከራ ቀን አንተ መጠጊያዬ ነህ።
18 አሳዳጆቼ ይፈሩ፥ እኔ ግን አልፈር፤ እነርሱ ይደንግጡ፥ እኔ ግን አልደንግጥ፤ ክፉንም ቀን አምጣባቸው፥ በሁለት እጥፍ ጥፋት አጥፋቸው።
19 እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል። ሂድ፥ የይሁዳም ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ ልጆች በር በኢየሩሳሌምም በሮች ሁሉ ቁም፤
20 እንዲህም በላቸው። በእነዚህ በሮች የምትገቡ፥ እናንተ የይሁዳ ነገሥታት፥ ይሁዳም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፥ በሰንበትም ቀን ሸክም አትሸከሙ፥ በኢየሩሳሌምም በሮች አታግቡ፥
22 ከቤቶቻችሁም በሰንበት ቀን ሸክምን አታውጡ፥ ሥራንም ሁሉ አትሥሩበት፤ አባቶቻችሁንም እንዳዘዝሁ የሰንበትን ቀን ቀድሱ።
23 እነርሱ ግን አልሰሙም ጆሮአቸውን አላዘነበሉም፥ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም አንገታቸውን አደነደኑ።
24 እኔን ፈጽሞ ብትሰሙ፤ ይላል እግዚአብሔር፥ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ባታገቡ፥ የሰንበትንም ቀን ብትቀድሱ ሥራንም ሁሉ ባትሠሩበት፥
25 በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መሳፍንት በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ እየተቀመጡ በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ እነርሱና መሳፍንቶቻቸው የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚቀመጡ ይገባሉ፥ ይህችም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች።
26 የሚቃጠለው መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትን የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም የምስጋናውንም መሥዋዕት ይዘው ከይሁዳ ከተሞች ከኢየሩሳሌምም ዙሪያ ከብንያምም አገር ከቈላውም ከደጋውም ከደቡብም ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ።
27 ነገር ግን የሰንበትን ቀን እንድትቀድሱ፥ በሰንበትም ቀን ሸክምን ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳትገቡ የነገርኋችሁን ባትሰሙኝ፥ በበሮችዋ ላይ እሳትን አነድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም አዳራሾች ትበላለች፥ አትጠፋም።