ምዕራፍ 8

እንዲህም ሆነ፤ ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ላይ ፈራጆች አደረጋቸው።
2 ፤ የበኵር ልጁም ስም ኢዮኤል፥ የሁለተኛውም ስም አብያ ነበረ። እነርሱም በቤርሳቤህ ይፈርዱ ነበር።
3 ፤ ልጆቹም በመንገዱ አልሄዱም፥ ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር።
4 ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና።
5 ፤ እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት።
6 ፤ የሚፈርድልንም ንጉሥ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው፤ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
7 ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ።
8 ፤ ከግብጽ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው እንግዶች አማልክት በማምለካቸው እንደ ሠሩት ሥራ ሁሉ እንዲሁ በአንተ ደግሞ ያደርጉብሃል።
9 ፤ አሁንም ቃላቸውን ስማ፤ ነገር ግን ጽኑ ምስክር መስክርባቸው፥ በእነርሱም ላይ የሚነግሠውን የንጉሡን ወግ ንገራቸው።
10 ፤ ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ንጉሥን ለፈለጉ ሕዝብ ነገራቸው።
11 ፤ እንዲህም አለ። በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፥ በሰረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ፤
12 ፤ ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ይሆናሉ።
13 ፤ ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቶ ቀማሚዎችና ወጥቤቶች አበዛዎችም ያደርጋቸዋል።
14 ፤ ከእርሻችሁና ከወይናችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል።
15 ፤ ከዘራችሁና ከወይናችሁም አሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል።
16 ፤ ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል።
17 ፤ ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ።
18 ፤ በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አልሰማችሁም።
19 ፤ ሕዝቡ ግን የሳሙኤልን ነገር ይሰማ ዘንድ እንቢ አለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይሁንልን፥
20 ፤ እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፥ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል አሉት።
21 ፤ ሳሙኤልም የሕዝቡን ቃል ሁሉ ሰማ፥ ለእግዚአብሔርም ተናገረ።
22 ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን። ቃላቸውን ስማ፥ ንጉሥም አንግሥላቸው አለው። ሳሙኤልም የእስራኤልን ሰዎች። እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ሂዱ አላቸው።