ምዕራፍ 17

ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን በይሁዳ ባለው በሰኮት አከማቹ፤ በሰኮትና በዓዜቃ መካከል በኤፌስደሚም ሰፈሩ።
2 ፤ ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ተከማቹ፥ በዔላ ሸለቆም ሰፈሩ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጉ ተሰለፉ።
3 ፤ ፍልስጥኤማውያንም በአንድ ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፥ እስራኤልም በሌላው ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም ሸለቆ ነበረ።
4 ፤ ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር የጌት ሰው ጎልያድ፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ፥ ዋነኛ ጀግና መጣ።
5 ፤ በራሱም የናስ ቍር ደፍቶ ነበር፥ ጥሩርም ለብሶ ነበር፤ የጥሩሩም ሚዛን አምስት ሺህ ሰቅል ናስ ነበረ።
6 ፤ በእግሮቹም ላይ የናስ ገምባሌ ነበረ፥ የናስም ጭሬ በትከሻው ላይ ነበረ።
7 ፤ የጦሩም የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅልያ ነበረ፤ የጦሩም ሚዛን ስድስት መቶ ሰቅል ብረት ነበረ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር።
8 ፤ እርሱም ቆሞ ወደ እስራኤል ጭፍሮች ጮኸ። ለሰልፍ ትሠሩ ዘንድ ለምን ወጣችሁ? እኔ ፍልስጥኤማዊ፥ እናንተም የሳኦል ባሪያዎች አይደላችሁምን? ለእናንተ አንድ ሰው ምረጡ፥ ወደ እኔም ይውረድ፤
9 ፤ ከእኔም ጋር ሊዋጋ ቢችል ቢገድለኝም፥ ባሪያዎች እንሆናችኋለን፤ እኔ ግን ባሸንፈው ብገድለውም፥ እናንተ ባሪያዎች ትሆኑናላችሁ፥ ለእኛም ትገዛላችሁ አለ።
10 ፤ ፍልስጥኤማዊውም። ዛሬ የእስራኤልን ጭፎሮች ተገዳደርኋቸው፤ እንዋጋ ዘንድ አንድ ሰው ስጡኝ አለ።
11 ፤ ሳኦልና እስራኤልም ሁሉ እንዲህ የሚላቸውን የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፥ ደነገጡም።
12 ፤ ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፤ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፤ ስምንትም ልጆች ነበሩት፤ በሳኦልም ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር።
13 ፤ የእሴይም ሦስቱ ታላላቆች ልጆቹ ሳኦልን ተከትለው ወደ ሰልፉ ሄደው ነበር፤ ወደ ሰልፉም የሄዱት የሦስቱ ልጆቹ ስም ይህ ነበረ፤ ታላቁ ኤልያብ ሁለተኛውም አሚናዳብ ሦስተኛውም ሣማ ነበረ።
14 ፤ ዳዊት የሁሉ ታናሽ ነበረ፤ ሦስቱም ታላላቆች ሳኦልን ተከትለው ነበር።
15 ፤ ዳዊትም የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር።
16 ፤ ፍልስጥኤማዊውም ጥዋትና ማታ ይቀርብ፥ አርባ ቀንም ይታይ ነበር።
17 ፤ እሴይም ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው። ከዚህ ከተጠበሰው እሸት አንድ የኢፍ መስፈሪያ እነዚህንም አሥር እንጀራዎች ለወንድሞችህ ውሰድ፥ ወደ ሰፈሩም ወደ ወንድሞችህ ፈጥነህ አድርሳቸው፤
18 ፤ ይህንም አሥሩን አይብ ወደ ሻለቃው ውሰደው፤ የወንድሞችህንም ደኅንነት ጠይቅ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ።
19 ፤ ሳኦልና እነርሱ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ በዔላ ሸለቆ ነበሩ።
20 ፤ ዳዊትም ማልዶ ተነሣ፥ በጎቹንም ለጠባቂ ተወ፥ እሴይም ያዘዘውን ይዞ ሄደ፤ ጭፍራውም ተሰልፎ ሲወጣ ለሰልፍም ሲጮኽ በሰረገሎች ወደ ተከበበው ሰፈር መጣ።
21 ፤ እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ፊት ለፊት ተሰላልፈው ነበር።
22 ፤ ዳዊትም ዕቃውን በዕቃ ጠባቂው እጅ አኖረው፥ ወደ ሠራዊቱም ሮጠ፥ የወንድሞቹንም ደኅንነት ጠየቀ።
23 ፤ እርሱም ሲነጋገራቸው፥ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለው ያ ዋነኛ ጀግና ፍልስጥኤማዊ የጌት ሰው ከፍልስጥኤማውያን ጭፍራ መካከል ወጣ፥ የተናገረውንም ቃል ተናገረ፤ ዳዊትም ሰማ።
24 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ሰውዮውን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው ከእርሱ ሸሹ።
25 ፤ የእስራኤልም ሰዎች። ይህን የወጣውን ሰው አያችሁትን? በእውነት እስራኤልን ሊገዳደር ወጣ፤ የሚገድለውንም ሰው ንጉሡ እጅግ ባለጠጋ ያደርገዋል፥ ልጁንም ይድርለታል፤ ያባቱንም ቤተ ሰብ በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያወጣቸዋል አሉ።
26 ፤ ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች። ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው ምን ይደረግለታል? የሕያውን አምላክ ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው።
27 ፤ ሕዝቡም። ለሚገድለው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ብለው እንደ ቀድሞው መለሱለት።
28 ፤ ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ የኤልያብም ቍጣ በዳዊት ላይ ነድዶ። ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኵራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል አለው።
29 ፤ ዳዊትም። እኔ ምን አደርግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን? አለ።
30 ፤ ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፥ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፤ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት።
31 ፤ ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፥ ለሳኦልም ነገሩት፤ ወደ እርሱም አስጠራው።
32 ፤ ዳዊትም ሳኦልን። ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፤ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያንን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ አለው።
33 ፤ ሳኦልም ዳዊትን። አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም አለው።
34 ፤ ዳዊትም ሳኦልን አለው። እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር።
35 ፤ በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር።
36 ፤ እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ፤ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል።
37 ፤ ዳዊትም። ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል አለ። ሳኦልም ዳዊትን። ሂድ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል አለው።
38 ፤ ሳኦልም ዳዊትን የገዛ ራሱን ልብስ አለበሰው፥ በራሱም ላይ የናስ ቍር ደፋለት፥ ጥሩርም አለበሰው።
39 ፤ ዳዊትም ሰይፉን በልብሱ ላይ ታጠቀ፥ ገናም አልፈተነውምና መሄድ ሞከረ። ዳዊትም ሳኦልን። አልፈተንሁትምና እንዲህ ብዬ መሄድ አልችልም አለው።
40 ፤ ዳዊትም አወለቀ። በትሩንም በእጁ ወሰደ፥ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፥ በእረኛ ኮረጆውም በኪሱ ከተታቸው፤ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፤ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ።
41 ፤ ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር።
42 ፤ ጎልያድም ዳዊትን ትኵር ብሎ አየው፤ ቀይ ብላቴና መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው።
43 ፤ ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን። በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን? አለው። ፍልስጥኤማዊውም በአምላኮቹ ስም ዳዊትን ረገመው።
44 ፤ ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን። ወደ እኔ ና፥ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ አለው።
45 ፤ ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው። አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።
46 ፤ እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፥ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፤
47 ፤ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።
48 ፤ ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ።
49 ፤ ዳዊትም እጁን ወደ ኮረጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፥ ወነጨፈውም፥ ፍልስጥኤማዊውንም ግምባሩን መታ፤ ድንጋዩም በግምባሩ ተቀረቀረ፥ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ።
50 ፤ ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ፤ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም።
51 ፤ ዳዊትም ሮጦ በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፤ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፥ ገደለውም፥ ራሱንም ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ዋናቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ሸሹ።
52 ፤ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እልል አሉ፥ ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጌትና እስከ አስቀሎና በርድረስ አሳደዱአቸው። ፍልስጥኤማውያንም ከሸዓራይም ጀምሮ እስከ ጌትና እስከ አቃሮን ድረስ በመንገድ ላይ የተመቱት ወደቁ።
53 ፤ የእስራኤልም ልጆች ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመልሰው ሰፈራቸውን በዘበዙ።
54 ፤ ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ጋሻ ጦሩን ግን በድንኳኑ ውስጥ አኖረው።
55 ፤ ሳኦልም ዳዊትን ወደ ፍልስጥኤማዊው ሲወጣ ባየው ጊዜ ለሠራዊቱ አለቃ ለአበኔር። አበኔር ሆይ፥ ይህ ብላቴና የማን ልጅ ነው? አለው። አበኔርም። ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! አላውቅም አለ።
56 ፤ ንጉሡም። ይህ ብላቴና የማን ልጅ እንደ ሆነ አንተ ጠይቅ አለ።
57 ፤ ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ አበኔር ወሰደው፥ ወደ ሳኦልም ፊት አመጣው፤ የፍልስጥኤማዊውንም ራስ በእጁ ይዞ ነበር።
58 ፤ ሳኦልም። አንተ ብላቴና፥ የማን ልጅ ነህ? አለው። ዳዊትም። እኔ የቤተ ልሔሙ የባሪያህ የእሴይ ልጅ ነኝ ብሎ መለሰ።