ምዕራፍ 20

ዳዊትም ከአርማቴም አገር ከነዋትዘራማ ሸሸ፥ ወደ ዮናታንም መጥቶ። ምን አደረግሁ? እኔንስ ለመግደል የሚፈልግ በአባትህ ፊት ጠማምነቴና ኃጢአቴ ምንድር ነው? ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ዮናታንም። ይህንስ ያርቀው፥ አትሞትም፤ እነሆ፥ አባቴ አስቀድሞ ለእኔ ሳይገልጥ ትልቅም ትንሽም ነገር ቢሆን አያደርግም፤ አባቴስ ይህን ነገር ለምን ይሰውረኛል? እንዲህ አይደለም አለው።
3 ፤ ዳዊትም። እኔ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘሁ አባትህ በእውነት ያውቃል፤ እርሱም። ዮናታን እንዳይከፋው አይወቅ ይላል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ያህል ቀርቶአል ብሎ ማለ።
4 ፤ ዮናታንም ዳዊትን። ነፍስህ የወደደችውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው።
5 ፤ ዳዊትም ዮናታንን አለው። እነሆ፥ ነገ መባቻ ነው፤ በንጉሥም አጠገብ ለምሳ አልቀመጥም፤ እስከ ሦስተኛው ቀን ማታ ድረስ በውጭ በሜዳ እንድሸሸግ አሰናብተኝ።
6 ፤ አባትህም ቢፈልገኝ። ለዘመዶቹ ሁሉ በዚያ በቤተ ልሔም የዓመት መሥዋዕት አላቸውና ዳዊት ወደ ከተማው ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለምኖኛል በለው።
7 ፤ እርሱም። መልካም ነው ቢል ለእኔ ለባሪያህ ደኅንነት ይሆናል፤ ቢቈጣ ግን ክፋት ከእርሱ ዘንድ በእኔ ላይ እንደ ተቈረጠች እወቅ።
8 ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከባሪያህ ጋር አድርገሃልና ለባሪያህ ቸርነት አድርግ፤ በደል ግን ቢገኝብኝ አንተ ግደለኝ፤ ለምን ወደ አባትህ ታደርሰኛለህ?
9 ፤ ዮናታንም። ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ከአባቴ ዘንድ ክፋት በላይህ እንደ ተቈጠረች ያወቅሁ እንደ ሆነ አልነግርህምን? አለ።
10 ፤ ዳዊትም ዮናታንን። አባትህ ስለ እኔ ክፉ ነገር የነገረህ እንደ ሆን ማን ይነግረኛል? አለው።
11 ፤ ዮናታንም ዳዊትን። ና ወደ ሜዳ እንውጣ አለው። ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ።
12 ፤ ዮናታንም ዳዊትን አለው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን፤ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ጊዜ አባቴን መርምሬ፥ እነሆ፥ በዳዊት ላይ መልካም ቢያስብ ልኬ እገልጥልሃለሁ፤
13 ፤ አባቴም በአንተ ላይ ክፋት ማድረግ ቢወድድ እኔም ባላስታውቅህ በደህና ትሄድ ዘንድ ባላሰናብትህ፥ እግዚአብሔር በዮናታን ይህን ያድርግ ይህንም ይጨምር፤ እግዚአብሔርም ከአባቴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን።
14 ፤ እኔም እንዳልሞት በሕይወቴ ዘመን የእግዚአብሔርን ቸርነት አድርግልኝ፤
15 ፤ ደግሞም እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ እያንዳንዱ ከምድር ባጠፋቸው ጊዜ ለዘላለም ቸርነትህን ከቤቴ አታርቀው።
16 ፤ ዮናታንም። እግዚአብሔር ከዳዊት ጠላቶች እጅ ይፈልገው ብሎ ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።
17 ፤ ዮናታንም ዳዊትን እንደ ነፍሱ ይወድድ ነበርና እንደ ገና ማለለት።
18 ፤ ዮናታንም አለው። ነገ መባቻ ነው፥ መቀመጫህም ባዶ ሆኖ ይገኛልና ትታሰባለህ።
19 ፤ ሦስት ቀንም ያህል ቆይ፤ ከዚህም በኋላ ፈጥነህ ውረድ፥ ነገሩም በተደረገበት ቀን ወደ ተሸሸግህበት ስፍራ ሂድ፥ በኤዜል ድንጋይም አጠገብ ቆይ።
20 ፤ እኔም በዓላማ ላይ እወረውራለሁ ብዬ ሦስት ፍላጻዎችን ወደ አጠገቡ እወረውራለሁ።
21 ፤ እነሆም። ሂድ ፍላጻዎችን ፈልግ ብዬ ብላቴናውን እልከዋለሁ፤ ብላቴናውንም። እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ይዘኸው ወደ እኔ ና ያልሁት እንደ ሆነ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! ለአንተ ደኅንነት ነውና ምንም የለብህም።
22 ፤ ብላቴናውን ግን። እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ያልሁት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔር አሰናብቶሃልና መንገድህን ሂድ።
23 ፤ አንተና እኔም ስለ ተነጋገርነው፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለዘላለም በመካከላችን ምስክር ነው።
24 ፤ ዳዊትም በሜዳው ተሸሸገ፤ መባቻም በሆነ ጊዜ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ።
25 ፤ ንጉሡም እንደ ቀድሞው በግንቡ አጠገብ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮናታንም ቆሞ ነበር፥ አበኔርም በሳኦል አጠገብ ተቀመጠ፤ የዳዊትም ስፍራ ባዶውን ነበረ።
26 ፤ ሳኦልም። አንድ ነገር ሆኖአል፥ ንጹሕም አይደለም፤ በእውነት ንጹሕ አይደለም ብሎ አስቦአልና በዚያን ቀን ምንም አልተናገረም።
27 ፤ ከመባቻም በኋላ በማግሥቱ በሁለተኛው ቀን የዳዊት ስፍራ ባዶውን ነበረ፤ ሳኦልም ልጁን ዮናታንን። የእሴይ ልጅ ትናንትና ወይም ዛሬ ግብር ሊበላ ያልመጣ ስለ ምን ነው? አለው።
28 ፤ ዮናታንም ለሳኦል። ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለመነኝ፤
29 ፤ እርሱም። ዘመዶቼ በከተማ ውስጥ መሥዋዕት አላቸውና፥ ወንድሜም ጠርቶኛልና እባክህ፥ አሰናብተኝ፤ አሁንም በዓይኖችህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ልሂድና ወንድሞቼን ልይ አለ፤ ስለዚህ ወደ ንጉሥ ሰደቃ አልመጣም ብሎ መለሰለት።
30 ፤ የሳኦልም ቍጣ በዮናታን ላይ ነደደና። አንተ የጠማማ ሴት ልጅ፥ የእሴይን ልጅ ለአንተ ማፈርያ ለእናትህም ኀፍረተ ሥጋ ማፈርያ እንደ መረጥህ እኔ አላውቅምን?
31 ፤ የእሴይም ልጅ በምድር ላይ በሕይወት በሚኖርበት ዘመን ሁሉ አንተና መንግሥትህ አትጸኑም፤ አሁንም የሞት ልጅ ነውና ልከህ አስመጣልኝ አለው።
32 ፤ ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል። ስለ ምን ይሞታል? ያደረገውስ ምንድር ነው? ብሎ መለሰለት።
33 ፤ ሳኦልም ሊወጋው ጦሩን ወረወረበት፤ ዮናታንም አባቱ ዳዊትን ፈጽሞ ሊገድለው እንደ ፈቀደ አወቀ።
34 ፤ አባቱ ዳዊትን ስላሳፈረው ዮናታን ስለ ዳዊት አዝኖአልና እጅግ ተቈጥቶ ከሰደቃው ተነሣ፥ በመባቻውም በሁለተኛ ቀን ግብር አልበላም።
35 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ዮናታን ከዳዊት ጋር ወደ ተቃጠረበት ቦታ ወደ ሜዳ ወጣ፥ ከእርሱም ጋር ታናሽ ብላቴና ነበረ።
36 ፤ ብላቴናውንም። ሮጠህ የምወረውራቸውን ፍላጻዎች ፈልግልኝ አለው። ብላቴናውም በሮጠ ጊዜ ፍላጻውን ወደ ማዶ ወረወረው።
37 ፤ ብላቴናውም ዮናታን ፍላጻውን ወደ ወረወረበት ስፍራ በመጣ ጊዜ ዮናታን። ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ።
38 ፤ ዮናታንም ደግሞ። ቶሎ ፍጠን፥ አትቆይ ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ፤ የዮናታንም ብላቴና ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው መጣ።
39 ፤ ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነገሩን ያውቁ ነበር እንጂ ብላቴናው ምንም አያውቅም ነበር።
40 ፤ ዮናታንም መሣርያውን ለብላቴናው ሰጥቶ። ወደ ከተማ ውሰድ አለው።
41 ፤ ብላቴናውም በሄደ ጊዜ ዳዊት ከስፍራው በደቡብ አጠገብ ተነሣ፥ በምድርም ላይ በግምባሩ ተደፋ፥ ሦስት ጊዜም ለሰላምታ ሰገደ፤ እየተላቀሱም እርስ በእርሳቸው ተሳሳሙ፥ ይልቁንም ዳዊት እጅግ አለቀሰ።
42 ፤ ዮናታንም ዳዊትን። በደኅና ሂድ፤ እነሆ፥ እኛ ሁለታችን በእኔና በአንተ፥ በዘሬና በዘርህ መካከል ለዘላለም እግዚአብሔር ይሁን ብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናል አለው። ዳዊትም ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ገባ።