ምዕራፍ 23

ለዳዊትም። እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ቅዒላን ይወጋሉ፥ አውድማውንም ይዘርፋሉ የሚል ወሬ ደረሰው።
2 ፤ ዳዊትም። ልሂድን? እነዚህንስ ፍልስጥኤማውያን ልምታን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም ዳዊትን። ሂድ፥ ፍልስጥኤማውያንን ምታ ቅዒላንም አድን አለው።
3 ፤ የዳዊትም ሰዎች። እነሆ፥ በዚህ በይሁዳ መቀመጥ እንፈራለን፥ ይልቁንስ በፍልስጥኤማውያን ጭፍሮች ላይ ወደ ቅዒላ ብንሄድ እንዴት ነው? አሉት።
4 ፤ ዳዊትም ደግሞ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም መልሶ። ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጣለሁና ተነሥተህ ወደ ቅዒላ ውረድ አለው።
5 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ቅዒላ ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፤ እንስሶቻቸውንም ማረኩ፥ በታላቅም አገዳደል ገደሉአቸው። ዳዊትም በቅዒላ የሚኖሩትን አዳነ።
6 ፤ እንዲህም ሆነ፤ የአቢሜሌክ ልጅ አብያታር ወደ ዳዊት ወደ ቅዒላ በኰበለለ ጊዜ ኤፉዱን ይዞ ወርዶ ነበር።
7 ፤ ሳኦልም ዳዊት ወደ ቅዒላ እንደ መጣ ሰማ፤ ሳኦልም። መዝጊያና መወርወሪያ ወዳለባት ከተማ ገብቶ ተገኝቶአልና እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶታል አለ።
8 ፤ ሳኦልም ወደ ቅዒላ ወርደው ይዋጉ ዘንድ፥ ዳዊትንና ሰዎቹንም ይከብቡ ዘንድ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ።
9 ፤ ዳዊትም ሳኦል ክፉን እንዳሰበበት አወቀ፤ ካሁኑን አብያታርንም። ኤፉዱን ወደዚህ አምጣ አለው።
10 ፤ ዳዊትም። የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ በእኔ ምክንያት ከተማይቱን ያጠፋ ዘንድ ሳኦል ወደ ቅዒላ ሊመጣ እንደሚፈልግ እኔ ባሪያህ ፈጽሜ ሰምቻለሁ።
11 ፤ የቅዒላ ሰዎች በእጁ አሳልፈው ይሰጡኛልን? ባሪያህስ እንደ ሰማ ሳኦል በውኑ ይወርዳልን? የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ እንድትነግረኝ እለምንሃለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ይወርዳል አለ።
12 ፤ ዳዊትም። የቅዒላ ሰዎች እኔንና ሰዎቼን በሳኦል እጅ አሳልፈው ይሰጡናልን? አለ። እግዚአብሔርም። አሳልፈው ይሰጡአችኋል ብሎ ተናገረ።
13 ፤ ዳዊትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ሰዎችም ተነሥተው ከቅዒላ ወጡ፥ መሄድም ወደሚችሉበት ሄዱ። ሳኦልም ዳዊት ከቅዒላ እንደ ሸሸ ሰማ፤ ስለዚህም ከመውጣት ቀረ።
14 ፤ ዳዊትም በምድረ በዳ በአምባ ውስጥ ይኖር ነበር፥ ከዚፍ ምድረ በዳም ባለው በተራራማው አገር ተቀመጠ፤ ሳኦልም ሁልጊዜ ይፈልገው ነበር፥ እግዚአብሔር ግን በእጁ አሳልፎ አልሰጠውም።
15 ፤ ዳዊትም ሳኦል ነፍሱን ሊፈልግ እንደ ወጣ አየ፤ ዳዊትም በዚፍ ምድረ በዳ በጥሻው ውስጥ ይኖር ነበር።
16 ፤ የሳኦልም ልጅ ዮናታን ተነሥቶ ወደ ዳዊት ወደ ጥሻው ስጥ ሄደ፤ እጁንም በእግዚአብሔር አጽንቶ።
17 ፤ የአባቴ የሳኦል እጅ አታገኝህምና አትፍራ፤ አንተም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፥ እኔም ከአንተ በታች ሁለተኛ እሆናለሁ፤ ይህን ደግሞ አባቴ ሳኦል ያውቃል አለው።
18 ፤ ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ዳዊትም በጥሻው ውስጥ ተቀመጠ፥ ዮናታንም ወደ ቤቱ ሄደ።
19 ፤ የዚፍ ሰዎችም ወደ ሳኦል ወደ ጊብዓ መጥተው። እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ደቡብ በኩል በኤኬላ ኮረብታ ላይ በጥሻ ውስጥ ባሉት አምባዎች በእኛ ዘንድ ተሸሽጎ የለምን?
20 ፤ አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ ትወርድ ዘንድ ነፍስህ እንደ ወደደች ውረድ፤ በንጉሡም እጅ እርሱን አሳልፎ ለመስጠት እኛ አለን አሉት።
21 ፤ ሳኦልም አለ። እናንተ ስለ እኔ አዝናችኋልና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረካችሁ ሁኑ፤
22 ፤ አሁንም ደግሞ ሂዱ፤ እርሱም እጅግ ተንኰለኛ እንደ ሆነ ሰምቻለሁና አጥብቃችሁ ፈልጉት፥ እግሩም የሚሄድበትን ስፍራ እዩና እወቁ፥ በዚያ ያየውንም ሰው አግኙ።
23 ፤ እርሱ የሚደበቅበትንና የሚሸሸግበትን ስፍራ እዩና እወቁ፥ በእርግጥም ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ከእናንተ ጋር እሄዳለሁ፤ በምድርም ውስጥ ቢሸሸግ በይሁዳ አእላፋት ሁሉ መካከል እፈልገዋለሁ።
24 ፤ እነዚያም ተነሥተው ከሳኦል በፊት ወደዚፍ ሄዱ፤ ዳዊትና ሰዎቹ ግን በየሴሞን ደቡብ በኩል በዓረባ በማዖን ምድረ በዳ ነበሩ።
25 ፤ ሳኦልና ሰዎቹም ሊፈልጉት ሄዱ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ወደ ዓለቱ ወርዶ በማዖን ምድረ በዳ ተቀመጠ፤ ሳኦልም ያንን በሰማ ጊዜ ዳዊትን በማዖን ምድረ በዳ አሳደደው።
26 ፤ ሳኦልም በተራራው በአንድ ወገን ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም በተራራው በሌላው ወገን ሄዱ። ሳኦልና ሰዎቹም ዳዊትንና ሰዎቹን ለመያዝ ከብበዋቸው ነበርና ዳዊት ከሳኦል ፊት ያመልጥ ዘንድ ፈጠነ።
27 ፤ ወደ ሳኦልም መልእክተኛ መጥቶ። ፍልስጥኤማውያን አገሩን ወርረውታልና ፈጥነህ ና አለው።
28 ፤ ሳኦልም ዳዊትን ማሳደድ ትቶ ተመለሰ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጋ ሄደ። ስለዚህ የዚህ ስፍራ ስም የማምለጥ ዓለት ተባለ።
29 ፤ ዳዊትም ከዚያ ወጥቶ በዓይንጋዲ አምባዎች ተቀመጠ።