ምዕራፍ 7

የቂርያትይዓሪም ሰዎችም መጥተው የእግዚአብሔርን ታቦት አወጡ፥ በኮረብታውም ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት አገቡት፤ የእግዚአብሔርም ታቦት እንዲጠብቅ ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት።
2 ፤ ታቦቱም በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ ወራቱ ረዘመ፥ ሀያ ዓመትም ሆነ፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ አዝኖ እግዚአብሔርን ተከተለ።
3 ፤ ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ። በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ እንግዶችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር አቅኑ፥ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ያድናችኋል ብሎ ተናገራቸው።
4 ፤ የእስራኤልም ልጆች በኣሊምንና አስታሮትን አራቁ፥ እግዚአብሔርንም ብቻ አመለኩ።
5 ፤ ሳሙኤልም። እስራኤልን ሁሉ ወደ ምጽጳ ሰብስቡ፥ ስለ እናንተም ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ አለ።
6 ፤ ወደ ምጽጳም ተሰበሰቡ፤ ውኃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሱ፥ በዚያም ቀን ጾሙ፥ በዚያም። እግዚአብሔርን በድለናል አሉ። ሳሙኤልም በእስራኤል ልጆች ላይ በምጽጳ ፈረደ።
7 ፤ ፍልስጥኤማውያንም የእስራኤል ልጆች ወደ ምጽጳ እንደ ተሰበሰቡ በሰሙ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን አለቆች በእስራኤል ላይ ወጡ፤ የእስራኤልም ልጆች ሰምተው ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ።
8 ፤ የእስራኤልም ልጆች ሳሙኤልን። ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ትጸልይልን ዘንድ አትታክት አሉት።
9 ፤ ሳሙኤልም አንድ የሚጠባ የበግ ጠቦት ወስዶ ለእግዚአብሔር ፈጽሞ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው፤ ሳሙኤልም ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው።
10 ፤ ሳሙኤልም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርግ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በዚያች ቀን በፍልስጥኤማውያን ላይ ታላቅ ነጐድጓድ አንጐደጐደ፥ አስደነገጣቸውም በእስራኤልም ፊት ድል ተመቱ።
11 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከምጽጳ ወጡ፥ ፍልስጥኤማውያንንም አሳደዱ፤ በቤትካር ታችም እስኪደርሱ ድረስ መቱአቸው።
12 ፤ ሳሙኤልም አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል አኖረው፤ ስሙንም። እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል ሲል አቤንኤዘር ብሎ ጠራው።
13 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተዋረዱ፥ ዳግመኛም ከዚያ ወዲያ ወደ እስራኤል ድንበር አልወጡም፤ በሳሙኤል ዕድሜ ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ነበረች።
14 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ከአስቀሎና ጀምሮ እስከ ጌት ድረስ ከእስራኤል የወሰዱአቸው ከተሞች ለእስራኤል ተመለሱ፤ እስራኤልም ድንበሩን ከፍልስጥኤማውያን እጅ አዳነ። በእስራኤልና በአሞራውያንም መካከል ዕርቅ ነበረ።
15 ፤ ሳሙኤልም በዕድሜው ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር።
16 ፤ በየዓመቱም ወደ ቤቴል ወደ ጌልገላ ወደ ምጽጳም ይዞር ነበር፤ በእነዚያም ስፍራዎች ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር።
17 ፤ ቤቱም በዚያ ነበረና ወደ አርማቴም ይመለስ ነበር፤ በዚያም በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።