ምዕራፍ 30

እንዲህም ሆነ፤ ዳዊትና ሰዎቹ በሦስተኛው ቀን ወደ ጺቅላግ በመጡ ጊዜ፥ አማሌቃውያን በደቡብ አገርና በጺቅላግ ላይ ዘምተው ነበር፥ ጺቅላግንም መትተው በእሳት አቃጥለዋት ነበር፤
2 ፤ ሴቶቹንና በውስጥዋም የነበሩትን ሁሉ ከታናሽ እስከ ታላቅ ድረስ ማርከው ነበር፤ ሁሉንም ወስደው መንገዳቸውን ሄዱ እንጂ አንድስ እንኳ አልገደሉም ነበር።
3 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ከተማ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ በእሳት ተቃጥላ፥ ሚስቶቻቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው አገኙ።
4 ፤ ዳዊት ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማልቀስ ኃይል እስኪያጡ ድረስ አለቀሱ።
5 ፤ የዳዊትም ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢግያ ተማርከው ነበር።
6 ፤ ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻቸው የሕዝቡ ሁሉ ልብ ተቈጥቶ ነበርና ሕዝቡ ሊወግሩት ስለ ተናገሩ ዳዊት እጅግ ተጨነቀ፤ ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ።
7 ፤ ዳዊትም የአቢሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን። ኤፉዱን አቅርብልኝ አለው፤ አብያታርም ኤፉዱን ለዳዊት አቀረበለት።
8 ፤ ዳዊትም። የእነዚህን ሠራዊት ፍለጋ ልከተልን? አገኛቸዋለሁን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም። ታገኛቸዋለህና፥ ፈጽመህም ምርኮውን ትመልሳለህና ፍለጋቸውን ተከተል ብሎ መለሰለት።
9 ፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ሄዱ፥ እስከ ቦሦር ወንዝ ድረስም መጡ፤ ከእነርሱም የቀሩት በዚያ ተቀመጡ።
10 ፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር ያሉት አራት መቶ ሰዎች አሳደዱ፤ ሁለቱ መቶ ሰዎች ግን የቦሦር ወንዝን መሻገር ደክመዋልና በኋላ ቀሩ።
11 ፤ በበረሀውም ውስጥ አንድ ግብጻዊ አግኝተው ወደ ዳዊት ይዘውት መጡ፤ እንጀራም ሰጡትና በላ፥ ውኃም አጠጡት፤
12 ፤ ከበለሱም ጥፍጥፍ ቁራጭና ሁለት የወይን ዘለላ ሰጡት፤ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንጀራ አልበላም ውኃም አልጠጣም ነበርና በበላ ጊዜ ነፍሱ ወደ እርሱ ተመለሰች።
13 ፤ ዳዊትም። አንተ የማን ነህ? ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። እኔ የአማሌቃዊ ባሪያ ግብጻዊ ብላቴና ነኝ፤ ከሦስት ቀንም በፊት ታምሜ ነበርና ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ።
14 ፤ እኛም በከሊታውያን ደቡብ፥ በይሁዳም ምድር፥ በካሌብም ደቡብ ላይ ዘመትን፤ ጺቅላግንም በእሳት አቃጠልናት አለ።
15 ፤ ዳዊትም። ወደ እነዚያ ሠራዊት ዘንድ ልትመራኝ ትወድዳለህን? አለው፤ እርሱም። እንዳትገድለኝ፥ ለጌታዬም እጅ አሳልፈህ እንዳትሰጠኝ በአምላክ ማልልኝ እንጂ ወደ እነዚያ ሠራዊት እመራሃለሁ አለ።
16 ፤ ወደ ታችም እንዲወርድ ባደረገው ጊዜ፥ እነሆ፥ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ከብዙ ምርኮ ሁሉ የተነሣ በልተው ጠጥተውም የበዓልም ቀን አድርገው በምድር ሁሉ ላይ ተበትነው ነበር።
17 ፤ ዳዊትም ከማታ ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ማታ ድረስ መታቸው፤ ከእነርሱም በግመል ተቀምጠው ከሸሹ ከአራት መቶ ጕልማሶች በቀር አንድ ያመለጠ የለም።
18 ፤ ዳዊትም አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣላቸው፥ ሁለቱንም ሚስቶቹን አዳነ።
19 ፤ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች፥ ከወሰዱትም ምርኮ ሁሉ፥ ታላቅም ሆነ ታናሽም ሆነ፥ ምንም የጐደለባቸው የለም፤ ዳዊትም ሁሉን አስጣለ።
20 ፤ ዳዊትም የበጉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፥ ከራሱም ከብት ፊት እየነዳ። ይህ የዳዊት ምርኮ ነው አለ።
21 ፤ ዳዊትም ደክመው ዳዊትን ይከተሉት ዘንድ ወዳልቻሉ፥ በቦሦር ወንዝ ወዳስቀራቸው ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትን ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሊቀበሉ ወጡ፤ ዳዊትም ወደ ሕዝቡ በቀረበ ጊዜ ደኅንነታቸውን ጠየቀ።
22 ፤ ከዳዊትም ጋር ከሄዱ ሰዎች ክፉዎቹና ምናምንቴዎቹ ሁሉ። እነዚህ ከእኛ ጋር አልመጡምና እየራሳቸው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ይሂዱ እንጂ ካስጣልነው ምርኮ ምንም አንሰጣቸውም አሉ።
23 ፤ ዳዊትም። ወንድሞቼ ሆይ፥ የጠበቀን በእኛም ላይ የመጣውን ጭፍራ በእጃችን አሳልፎ የሰጠን እግዚአብሔር በሰጠን ነገር እንዲህ አታድርጉ፤
24 ፤ ይህንስ ነገ ማን ይሰማችኋል? ነገር ግን የተዋጉትና ዕቃውን የጠበቁት እድል ፈንታ እኩል ይሆናል፥ አንድነት ይካፈላሉ አለ።
25 ፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ለእስራኤል ሥርዓትና ፍርድ አደረገው።
26 ፤ ዳዊትም ወደ ጺቅላግ በመጣ ጊዜ ለዘመዶቹ ለይሁዳ ሽማግሌዎች። እነሆ ከእግዚአብሔር ጠላቶች ምርኮ በረከትን ተቀበሉ ብሎ ከምርኮው ሰደደላቸው።
27 ፤ በቤቴል ለነበሩ፥ በራሞት በደቡብ ለነበሩ
28 ፤ በየቲር ለነበሩ፥ በአሮዔር ለነበሩ፥ በሢፍሞት ለነበሩ፥ በኤሽትሞዓ ለነበሩ፥
29 ፤ በቀርሜሎስ ለነበሩ፥ በይረሕምኤላውያንና በቄናውያን ከተሞችም ለነበሩ፥
30 ፤ በሔርማ ለነበሩ፥ በቦራሣን ለነበሩ፥ በዓታክ ለነበሩ፥ በኬብሮን ለነበሩ፥
31 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም በተመላለሱበት ስፍራ ለነበሩ ሰዎች ሁሉ ላከ።