ምዕራፍ 13

ሳኦልም በእስራኤል ላይ ሁለት ዓመት ከነገሠ በኋላ፥
2 ፤ ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎች ከእስራኤል መረጠ፤ ሁለቱም ሺህ በማክማስና በቤቴል ተራራ ከሳኦል ጋር ነበሩ፥ አንዱም ሺህ በብንያም ጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ፤ የቀረውንም ሕዝብ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ አሰናበተ።
3 ፤ ዮናታንም በናሲብ ውስጥ የነበረውን የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መታ፥ ፍልስጥኤማውያንም ያን ሰሙ፤ ሳኦልም። ዕብራውያን ይስሙ ብሎ በአገሩ ሁሉ ቀንደ መለከት ነፋ።
4 ፤ እስራኤልም ሁሉ ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ እንደ መታ፥ ደግሞም እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ተጸየፉ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ።
5 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ተሰበሰቡ፤ ሠላሳ ሺህ ሰረገሎች ስድስትም ሺህ ፈረሰኞች በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበሩ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በምሥራቅ በኩል በማክማስ ሰፈሩ።
6 ፤ ሕዝቡም ተጨንቀው ነበርና የእስራኤል ሰዎች በጭንቀት እንዳሉ ባዩ ጊዜ ሕዝቡ በዋሻና በእሾህ ቍጥቋጦ በገደልና በግንብ በጕድጓድም ውስጥ ተሸሸጉ።
7 ፤ ከዕብራውያንም ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ፤ ሳኦል ግን ገና በጌልገላ ነበረ፥ ሕዝቡም ሁሉ ተንቀጥቅጠው ተከተሉት።
8 ፤ ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ጊዜ ሰባት ቀን ቆየ፤ ሳሙኤል ግን ወደ ጌልገላ አልመጣም፥ ሕዝቡም ከእርሱ ተለይተው ተበታተኑ።
9 ፤ ሳኦልም። የሚቃጠል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት አምጡልኝ አለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ።
10 ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በፈጸመ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲመርቀው ሊገናኘው ወጣ።
11 ፤ ሳሙኤልም። ያደረግኸው ምንድር ነው? አለ። ሳኦልም። ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፥ አንተም በቀጠሮው እንዳልመጣህ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ማክማስ እንደ ተሰበሰቡ አየሁ፤
12 ፤ ሰለዚህ። ፍልስጥኤማውያን አሁን ወደ ጌልገላ ይወርዱብኛል፥ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም አልሁ፤ ስለዚህም ሳልታገሥ የሚቃጠልን መሥዋዕት አሳረግሁ አለ።
13 ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን። አላበጀህም፤ አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጽንቶልህ ነበረ።
14 ፤ አሁንም መንግሥትህ አይጸናም፤ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል፤ እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዞታል አለው።
15 ፤ ሳሙኤልም ከጌልገላ ተነሥቶ መንገዱን ሄደ፤ የቀሩትም ሕዝብ ሳኦልን ተከተለው ሰልፈኞቹን ሊገናኙ ሄዱ። ከጌልገላም ተነሥተው ወደ ብንያም ጊብዓ መጡ፤ ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ስድስት መቶም የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ።
16 ፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ከእነርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ በብንያም ጊብዓ ተቀመጡ፤ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ ሰፈሩ።
17 ፤ ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር ማራኪዎች በሦስት ክፍል ሆነው ወጡ፤ አንዱም ክፍል በዖፍራ መንገድ ወደ ሦጋል ምድር ሄደ።
18 ፤ ሁለተኛው ክፍል ወደ ቤት ሖሮን መንገድ ዞረ፤ ሦስተኛውም ክፍል በበረሃው አጠገብ ባለው ወደ ስቦይም ሸለቆ በሚመለከተው በዳርቻ መንገድ ዞረ።
19 ፤ ፍልስጥኤማውያንም። ዕብራውያን ሰይፍና ጦር እንዳይሠሩ ብለው ነበርና በእስራኤል ምድር ሁሉ ብረተ ሠሪ አልተገኘም።
20 ፤ እስራኤልም ሁሉ የማረሻውን ጫፍና ማጭዱን መጥረቢያውንና መቆፈሪያውን ይስል ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርድ ነበር።
21 ፤ ለማረሻው ጫፍና ለመቆፈሪያው ዋጋው የሰቅል ከ3 እጅ 2ቱ እጅ ነበረ። መጥረቢያውንም ለማሳል መውጊያውንም ለማበጀት ዋጋው የሰቅል ከ3 እጅ 1ዱ እጅ ነበረ።
22 ፤ ስለዚህም በሰልፍ ቀን ሰይፍና ጦር ከሳኦልና ከዮናታን ጋር በነበሩ ሕዝብ ሁሉ እጅ አልተገኘም፤ ብቻ በሳኦልና በልጁ በዮናታን ዘንድ ተገኘ። የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ ወደ ማክማስ መተላለፊያ ወጡ።
23