መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ
ምዕራፍ 3
ብላቴናውም ሳሙኤል በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር፤ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ፤ ራእይም አይገለጥም ነበር።
2 ፤ በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ ጀምረው ነበር።
3 ፤ ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ፥ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ሳለ፥
4 ፤ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፤ እርሱም። እነሆኝ አለ።
5 ፤ ወደ ዔሊም ሮጠ። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም። አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ አለው። ሄዶም ተኛ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ። ሳሙኤል ሆይ ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም። ልጄ ሆይ፥ አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ ብሎ መለሰ።
7 ፤ ሳሙኤል ግን ገና እግዚአብሔርን አላወቀም ነበር፥ የእግዚአብሔርም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር።
8 ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ ጠራው። እርሱም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለ። ዔሊም እግዚአብሔር ብላቴናውን እንደ ጠራው አስተዋለ።
9 ፤ ዔሊም ሳሙኤልን። ሄደህ ተኛ ቢጠራህም። አቤቱ፥ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር በለው አለው። ሳሙኤልም ሄዶ በስፍራው ተኛ።
10 ፤ እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም። ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም። ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለው።
11 ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። እነሆ፥ የሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገርን በእስራኤል አደርጋለሁ።
12 ፤ በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ አወርዳለሁ፤ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ።
13 ፤ ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤት ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ።
14 ፤ ስለዚህም የዔሊ ቤት ኃጢአት በመሥዋዕትና በቍርባን ለዘላለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ።
15 ፤ ሳሙኤልም እስኪነጋ ተኛ፥ ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ። ሳሙኤልም ራእዩን ለዔሊ መንገር ፈራ።
16 ፤ ዔሊም ሳሙኤልን ጠርቶ። ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥ አለ፤ እርሱም። እነሆኝ አለ።
17 ፤ እርሱም። እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድር ነው? ከእኔ አትሸሽግ፤ ከነገረህ ነገር ሁሉ የሸሸግኸኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፥ እንዲህም ይጨምርብህ አለው።
18 ፤ ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፥ አንዳችም አልሸሸገውም። ዔሊም። እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።
19 ፤ ሳሙኤልም አደገ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከቃሉም አንዳች በምድር ላይ አይወድቀም ነበር።
20 ፤ እስራኤልም ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ነቢይ ይሆን ዘንድ የታመነ እንደ ሆነ አወቀ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ በሴሎ ተገለጠ፤ እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ቃል ለሳሙኤል በሴሎ ይገለጥ ነበር። የሳሙኤልም ቃል ለእስራኤል ሁሉ ደረሰ።