ምዕራፍ 8

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን፥ ልብሱንም፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ለኃጢአት መሥዋዕትም የሆነውን ወይፈን፥ ሁለቱንም አውራ በጎች፥ የቂጣውንም እንጀራ ሌማት ውሰድ፤
3 ፤ ማኅበሩንም ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስባቸው።
4 ፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩ ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰቡ።
5 ፤ ሙሴም ማኅበሩን። እግዚአብሔር ይደረግ ዘንድ ያዘዘው ነገር ይህ ነው አላቸው።
6 ፤ ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፥ በውኃም አጠባቸው።
7 ፤ ሸሚዝም አለበሰው፥ በመታጠቂያም አስታጠቀው፥ ቀሚስም አለበሰው፥ ኤፉድም ደረበለት፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቋድ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ አሰረው።
8 ፤ የደረት ኪስ በእርሱ ላይ አደረገ፤ በደረቱ ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረበት።
9 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ መጠምጠሚያውን አደረገ፤ በመጠምጠሚያውም ላይ በፊቱ በኩል የተቀደሰውን አክሊል፥ ቅጠል የሚመስለውን የወርቅ ምልክት፥ አደረገ።
10 ፤ ሙሴም የቅብዓቱን ዘይት ወሰደ፥ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሳቸው።
11 ፤ ከእርሱም በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀባ።
12 ፤ ከቅብዓቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፥ ይቀድሰውም ዘንድ ቀባው።
13 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የአሮንን ልጆች አቀረበ፥ ቀሚሶችንም አለበሳቸው፥ በመታጠቂያም አስታጠቃቸው፥ ቆብም ደፋባቸው።
14 ፤ የኃጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኃጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ።
15 ፤ አረደውም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፥ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፥ ያስተሰርይለትም ዘንድ ቀደሰው።
16 ፤ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች ስባቸውንም ወሰደ፤ ሙሴም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።
17 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቁርበቱንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ።
18 ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ።
19 ፤ አረደውም፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው።
20 ፤ አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን ብልቶቹንም ስቡንም አቃጠለ።
21 ፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ሙሴም አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤ ይህ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ።
22 ፤ ለቅድስናም የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ።
23 ፤ አረደውም፤ ሙሴን ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት አስነካው።
24 ፤ የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀን እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ አስነካ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ።
25 ፤ ስቡንና ላቱን፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች ስባቸውንም፥ ቀኝ ወርቹንም ወሰደ፤
26 ፤ በእግዚአብሔር ፊት ካለው ከቂጣው እንጀራ ሌማት አንድ የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖራቸው።
27 ፤ ሁሉንም በአሮንና በልጆቹ እጆች ላይ አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዛቸው።
28 ፤ ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ በመሠዊያው በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው፤ የጣፋጭ ሽታ መቀደሻ ነበረ። እርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቁርባን ነበረ።
29 ፤ ሙሴም ፍርምባውን ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዘው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ይህ ለቅድስና ከታረደው አውራ በግ የሙሴ እድል ፈንታ ሆነ።
30 ፤ ሙሴም ከቅብዓቱ ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ከደሙ ወስዶ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ በልጆቹና በልጆቹ ልብስ ላይ ረጨው፤ አሮንንና ልብሱንም፥ ልጆቹንም የልጆቹንም ልብስ ቀደሰ።
31 ፤ ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አላቸው። ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉ፤ አሮንና ልጆቹ ይበሉታል ብዬ እንዳዘዝሁ በዚያ እርሱንና በሌማቱ ያለውን የቅድስናውን እንጀራ ብሉ።
32 ፤ ከሥጋውና ከእንጀራውም የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ።
33 ፤ ሰባት ቀን ይክናችኋልና የክህነታችሁ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሰባት ቀን ከማኅበሩ ድንኳን ደጃፍ አትውጡ።
34 ፤ በዚህ ቀን እንደ ተደረገ ለእናንተ ለማስተስረያ ይደረግ ዘንድ እንዲሁ እግዚአብሔር አዘዘ።
35 ፤ እግዚአብሔር እንዲሁ አዝዞኛልና እንዳትሞቱ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሌሊቱንና ቀኑን ሰባት ቀን ተቀመጡ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓት ጠብቁ።
36 ፤ አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።