ምዕራፍ 22

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ የእስራኤል ልጆች ለእኔ ከሚቀድሱአቸው ከቅዱሳን ነገሮች ራሳቸውን እንዲለዩ፥ የተቀደሰውንም ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
3 ፤ እንዲህ በላቸው። ማናቸውም ሰው ከዘራችሁ በትውልዳችሁ ርኵሰት እያለበት የእስራኤል ልጆች ለእግዚአብሔር ወደሚቀድሱት ወደ ቅዱስ ነገር ቢቀርብ፥ ያ ሰው ከፊቴ ተለይቶ ይጥፋ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
4 ፤ ከአሮን ዘር ለምጽ ወይም ፈሳሽ ነገር ያለበት ሁሉ ንጹሕ እስኪሆን ድረስ ከተቀደሰው አይብላ። ከበድንም የተነሣ ርኩስ የሆነውን፥ ወይም ዘሩ ከእርሱ የሚፈስስበትን የሚነካ፥
5 ፤ ወይም የሚያረክሰውን ተንቀሳቃሽ፥ ወይም በሁሉ ዓይነት የረከሰውን ሰው የሚነካ፥
6 ፤ እነዚህን ሁሉ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ገላውን በውኃ ካልታጠበ ከተቀደሰው አይብላ።
7 ፤ ፀሐይም በገባች ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ እንጀራው ነውና ከተቀደሰው ይብላ።
8 ፤ በእርሱም እንዳይረክስ፥ የሞተውን አውሬም የሰበረውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
9 ፤ ቢያረክሱአት እንዳይሞቱ ስለ እርስዋም ኃጢአትን እንዳይሸከሙ፥ ሕግን ይጠብቁ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
10 ፤ ልዩ ሰው ከተቀደሰው አይብላ የካህኑም እንግዳ ደመወዘኛውም ከተቀደሰው አይብላ።
11 ፤ ካህኑ ግን በገንዘቡ ባሪያ ቢገዛ እርሱ ይብላው፤ በቤቱም የተወለዱት ከእንጀራው ይብሉ።
12 ፤ የካህንም ልጅ ከልዩ ሰው ጋር ብትጋባ፥ እርስዋ ከተቀደሰው ቍርባን አትብላ።
13 ፤ የካህን ልጅ ግን ባልዋ ቢሞት፥ ወይም ብትፋታ፥ ልጅም ባይኖራት፥ በብላቴንነትዋ እንደ ነበረች ወደ አባትዋ ቤት ብትመለስ፥ ከአባትዋ እንጀራ ትብላ፤ ልዩ ሰው ግን ከእርሱ አይብላ።
14 ፤ ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ከተቀደሰው ቢበላ አምስተኛ እጅ ጨምሮ የተቀደሰውን ለካህኑ ይስጥ።
15
16 ፤ የምቀድሳቸውም እግዚአብሔር እኔ ነኝና ከተቀደሰው በበሉ ጊዜ ኃጢአትንና በደልን እንዳይሸከሙ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡትን በእስራኤል ልጆች ዘንድ የተቀደሰውን ነገር አያርክሱ።
17 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
18 ፤ ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእስራኤል ቤት ወይም ከእናንተ መካከል ከሚቀመጡት እንግዶች ማናቸውም ሰው ስእለቱን ሁሉ፥ በፈቃዱም የሚያቀርበውን ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበውን ቍርባን ቢያቀርብ፥
19 ፤ ይሠምርላችሁ ዘንድ ከበሬ ወይም ከበግ ወይም ከፍየል ነውር የሌለበትን ተባቱን አቅርቡ።
20 ፤ ነገር ግን አይሠምርላችሁምና ነውር ያለበትን አታቅርቡ።
21 ፤ ማናቸውም ሰው ስእለቱን ለመፈጸም ወይም በፈቃዱ ለማቅረብ የደኅንነትን መሥዋዕት፥ ወይም በሬን ወይም በግን፥ ለእግዚአብሔር ቢያቀርብ፥ ይሠምርለት ዘንድ ፍጹም ይሁን፥ ነውርም አይሁንበት።
22 ፤ ዕውር ወይም ሰባራ ወይም ጕንድሽ ወይም የሚመግል ቍስል ያለበት ወይም እከካም ወይም ቋቍቻም ቢሆን፥ እነዚህን ሁሉ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ እነዚህም ለእሳት ቍርባን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር አታሳርጉ።
23 ፤ በሬው ወይም በጉ የተጨመረበት ወይም የጐደለበት ነገር ቢሆን፥ ለፈቃድ መሥዋዕት ማቅረብ ትችላለህ፤ ለስእለት ግን አይሠምርም።
24 ፤ የተሰነጋውን ወይም የተቀጠቀጠውን ወይም የተሰበረውን ወይም የተቈረጠውን ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ በምድራችሁም እነዚህን አትሠዉ።
25 ፤ ከእነዚህም ከእንግዳ ሰው እጅ ለአምላካችሁ እንጀራ አታቅርቡ፤ ርኵሰትም ነውርም አለባቸውና አይሠምሩላችሁም።
26 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
27 ፤ በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ሲወለድ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፤ በስምንተኛውም ቀን ከዚያም በላይ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን የሠመረ ይሆናል።
28 ፤ ላም ወይም በግ ብትሆን እርስዋንና ልጅዋን በአንድ ቀን አትረዱ።
29 ፤ የምስጋናንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሠዉ እንዲሠምርላችሁ ሠዉለት።
30 ፤ በዚያው ቀን ይበላል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አትተዉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
31 ፤ ትእዛዛቴን ጠብቁ፥ አድርጉትም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
32 ፤ የተቀደሰውንም ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ግን በእስራኤል ልጆች መካከል እቀደሳለሁ፤
33 ፤ የምቀድሳችሁ፥ አምላካችሁም እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።