ምዕራፍ 10

የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ።
2 ፤ እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ።
3 ፤ ሙሴም አሮንን። እግዚአብሔር። ወደ እኔ በሚቀርቡ እቀድሳለሁ፥ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከብራለሁ ብሎ የተናገረው ይህ ነው አለው፤ አሮንም ዝም አለ
4 ፤ ሙሴም የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ። ቅረቡ፥ ወንድሞቻችሁንም ከመቅደሱ ፊት አንሥታችሁ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዱአቸው አላቸው።
5 ፤ እነርሱም ቀርበው አነሡአቸው፥ ሙሴም እንዳለ በቀሚሳቸው ከሰፈር ወደ ውጭ ወሰዱአቸው።
6 ፤ ሙሴም አሮንን፥ ልጆቹንም አልዓዛርንና ኢታምርን። እንዳትሞቱ በማኅበሩም ሁሉ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ራሳችሁን አትንጩ፥ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ እግዚአብሔር ስላቃጠለው ማቃጠል ግን ወንድሞቻችሁ የእስራኤል ቤት ሁሉ ያልቅሱ።
7 ፤ የእግዚአብሔር የቅብዓት ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትወጡም አላቸው። እንደ ሙሴ ቃልም አደረጉ።
8 ፤ እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
9 ፤ እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን ነገር ሁሉ አትጠጡ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤
10 ፤ በተቀደሰውና ባልተቀደሰው፥ በርኩሱና በንጹሑም መካከል ትለያላችሁ፤
11 ፤ እግዚአብሔርም በሙሴ ቃል የነገራቸውን ሥርዓት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ታስተምራላችሁ።
12 ፤ ሙሴም አሮንን፥ የተረፉለትንም ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን አላቸው። ቅዱስ ቅዱሳን ነውና ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቁርባን የቀረውን የእህሉን ቁርባን ውሰዱ፥ ቂጣም አድርጋችሁ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት እግዚአብሔርም እንዲህ አዞኛል፥
13 ፤ ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቁርባን ለአንተም ለልጆችህም የተሰጠ ሥርዓት ነውና በቅዱስ ስፍራ ትበሉታላችሁ።
14 ፤ እነዚህም ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕቶች ለአንተና ለልጆችህ ሥርዓት እንዲሆኑ ስለ ተሰጡ፥ የሚወዘወዘውን ፍርምባ፥ የሚነሣውንም ወርች አንተ፥ ከአንተ ጋርም ልጆችህ፥ ሴቶች ልጆችህም በንጹሕ ስፍራ ትበላላችሁ።
15 ፤ የሚነሣውን ወርች የሚወዘወዘውንም ፍርምባ በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን እንዲወዘውዙ የእሳት ቁርባን ከሆነው ስብ ጋር ያመጣሉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ለአንተ ከአንተ ጋርም ለልጆችህ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል።
16 ፤ ሙሴም የኃጢያቱን መሥዋዕት ፍየል እጅግ ፈለገው፥ እነሆም ተቃጥሎ ነበር፤ ሙሴም የቀሩትን የአሮንን ልጆች አልአዛርንና ኢታምርን ተቈጥቶ።
17 ፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነውና፥ የሕዝቡንም ኃጢያት እንድትሸከሙ፥ በእግዚአብሔርም ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ለእናንተ ሰጥቶታልና ስለ ምን የኃጢያትን መሥዋዕት በቅዱሱ ስፍራ አልበላችሁም?
18 ፤ እነሆ ደሙን ወደ መቅደሱ ውስጥ አላገባችሁትም፤ እኔ እንዳዘዝሁ በቅዱሱ ስፍራ ውስጥ ትበሉት ዘንድ ይገባችሁ ነበር አላቸው።
19 ፤ አሮንም ሙሴን። እነሆ ዛሬ የኃጢያታቸውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፤ ይህም ሁሉ ደረሰብኝ፤ ዛሬስ የኃጢያት መሥዋዕት በበላሁ ኖሮ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ኖሮአልን? አለው።
20 ፤ ሙሴም ሰማ በፊቱም መልካም ሆነ።