ምዕራፍ 7

የበደል መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነው።
2 ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት ስፍራ የበደሉን መሥዋዕት ያርዱታል፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጨዋል።
3 ፤ ስቡንም ሁሉ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ያቀርበዋል።
4 ፤ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ይወስዳል።
5 ፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱ የበደል መሥዋዕት ነው።
6 ፤ ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤ በተቀደሰ ስፍራ ይበሉታል፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነው።
7 ፤ የኃጢአት መሥዋዕት እንደ ሆነ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ለሁለቱ አንድ ሕግ ነው፤ በእርሱ የሚያስተሰርይ ካህን ይወስደዋል።
8 ፤ የማናቸውንም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ካህን ያቀረበው የሚቃጠለው መሥዋዕት ቁርበት ለዚያው ካህን ይሆናል።
9 ፤ በእቶን የተጋገረው የእህል ቍርባን ሁሉ፥ በመቀቀያም ወይም በምጣድ የበሰለው ሁሉ ለሚያቀርበው ካህን ይሆናል።
10 ፤ በዘይትም የተለወሰው ወይም የደረቀው የእህል ቍርባን ሁሉ ለአሮን ልጆች ሁሉ ይሆናል፤ ለሁሉም ይሆናል።
11 ፤ ሰው ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው።
12 ፤ ለምስጋና ቢያቀርበው፥ ከምስጋናው መሥዋዕት ጋር በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ በዘይትም የተለወሰ መልካም ዱቄት ያቀርባል።
13 ፤ ለምስጋና የሚሆነውን የደኅንነት መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ እርሾ ያለበትን ኅብስት ያቀርባል።
14 ፤ ከቍርባኑም ሁሉ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን እንዲሆን ከእነርሱ አንዱን ያነሣል። እርሱም የደኅንነትን መሥዋዕት ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል።
15 ፤ ለምስጋና የሚሆነው የደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ በሚቀርብበት ቀን ይበሉታል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አያድርም።
16 ፤ የቍርባኑም መሥዋዕት የስእለት ወይም የፈቃድ ቢሆን፥ መሥዋዕቱ በሚቀርብበት ቀን ይብሉት፤ ከእርሱም የቀረውን በነጋው ይብሉት፤
17 ፤ ከመሥዋዕቱም ሥጋ እስከ ሦስተኛው ቀን የሚቆየው በእሳት ይቃጠላል።
18 ፤ በሦስተኛው ቀን ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ አይሠምርም፤ ላቀረበው ሰው የተጠላ ይሆንበታል እንጂ ቍርባን ሆኖ አይቈጠርለትም፤ ከእርሱም ቢበላ ኃጢአቱን ይሸከማል።
19 ፤ ርኩስ ነገር የሚነካውን ሥጋ አይብሉት፤ በእሳት ይቃጠል። ንጹሕ የሆነ ሰው ሁሉ ግን ከሥጋው ይብላ።
20 ፤ ሰውም የረከሰ ቢሆን፥ ለእግዚአብሔርም ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።
21 ፤ ማናቸውንም ርኵስ ነገር ቢነካ፥ የሰውን ወይም የረከሰን እንስሳ ወይም ሌላውን የተጠላ ርኩስን ቢነካ፥ ለእግዚአብሔርም ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።
22 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
23 ፤ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። የበሬ ወይም የበግ ወይም የፍየል ስብ ከቶ አትብሉ።
24 ፤ የሞተውን ስብ፥ አውሬ የሰበረውንም ስብ ለሌላ ተግባር አድርጉት፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም አትብሉ፤
25 ፤ ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ከእንስሳ ስብ የሚበላ ሁሉ፥ ያ የበላ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና።
26 ፤ በማደሪያዎቻችሁም ሁሉ የወፍ ወይም የእንስሳ ደም ቢሆን አትብሉ።
27 ፤ ደም የሚበላ ሰው ሁሉ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ።
28 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
29 ፤ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። ለእግዚአብሔር የደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ቍርባኑን ለእግዚአብሔር ከደኅንነቱ መሥዋዕት ያመጣል።
30 ፤ የእርሱ እጆች ለእግዚአብሔር የእሳቱን ቍርባን ያመጣሉ፤ ፍርምባው በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ይወዘውዝ ዘንድ ስቡንና ፍርምባውን ያመጣል።
31 ፤ ካህኑም ስቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል፤ ፍርምባውም ለአሮንና ለልጆቹ ይሁን።
32 ፤ ከደኅንነት መሥዋዕታችሁ ቀኝ ወርቹን ለማንሣት ቍርባን እንዲሆን ለካህኑ ትሰጡታላችሁ።
33 ፤ ከአሮንም ልጆች የደኅንነትን መሥዋዕት ደሙንና ስቡን ለሚያቀርብ ለእርሱ ቀኝ ወርቹ እድል ፈንታው ይሆናል።
34 ፤ የሚወዘወዘውን ፍርምባና የሚነሣውን ወርች ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕታቸው ወስጄአለሁ፥ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ለዘላለም እድል ፈንታ እንዲሆን ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ሰጥቼአቸዋለሁ።
35 ፤ እግዚአብሔርን በክህነት ያገለግሉት ዘንድ ባቀረባቸው ቀን ለእግዚአብሔር ከሆነ ከእሳት ቍርባን የአሮንና የልጆቹ እድል ፈንታ ይህ ነው።
36 ፤ ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም እድል ፈንታቸው እንዲሆን በቀባቸው ቀን የእስራኤል ልጆች ይሰጡአቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው።
37 ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን፥ የኃጢአትና የበደል መሥዋዕት፥ የቅድስናና የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው።
38 ፤ እግዚአብሔር በሲና ምድረ በዳ ቍርባናቸውን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ባዘዘ ጊዜ በሲና ተራራ ለሙሴ ያዘዘው ይህ ነው።