ምዕራፍ 12

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ሴት ብታረግዝ ወንድ ልጅም ብትወልድ፥ ሰባት ቀን ያህል የረከሰች ናት፤ እንደ ሕመምዋ መርገም ወራት ትረክሳለች።
3 ፤ በስምንተኛውም ቀን ልጁ ከሥጋው ሸለፈት ይገረዝ።
4 ፤ ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቀመጥ፤ የመንጻትዋ ቀንም እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰን ነገር አትንካ፥ ወደ መቅደስም አትግባ።
5 ፤ ሴት ልጅም ብትወልድ እንደ መርገምዋ ወራት ሁለት ሳምንት ያህል የረከሰች ናት፤ ከደምዋም እስክትነጻ ድረስ ስድሳ ስድስት ቀን ትቀመጥ።
6 ፤ የመንጻትዋ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ፥ ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ፥ የአንድ ዓመት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ የርግብም ግልገል ወይም ዋኖስ ለኃጢአት መሥዋዕት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ታምጣለት።
7 ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል ያስተሰርይላትማል፤ ከደምዋም ፈሳሽ ትነጻለች። ወንድ ወይም ሴት ለምትወልድ ሴት ሕጉ ይህ ነው።
8 ፤ ጠቦት ለማምጣት ገንዘብዋ ያልበቃት እንደ ሆነ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ሌላውንም ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባለች፤ ካህኑም ያስተሰርይላታል፥ እርስዋም ትነጻለች።