ምዕራፍ 21

እግዚአብሔርም ሙሴን። ለካህናቱ ለአሮን ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው አለው። ማንም ሰው ከሕዝቡ ስለ ሞተው፥
2 ፤ ከሚቀርበው ዘመዱ፥ ከእናቱ፥ ወይም ከአባቱ፥ ወይም ከወንድ ልጁ፥ ወይም ከሴት ልጁ፥ ወይም ከወንድሙ በቀር አይርከስ።
3 ፤ ወይም የቀረበችው ያልተጋባች ድንግል እኅቱ በእርስዋ ይርከስ።
4 ፤ የሕዝቡ አለቃ ራሱን ያጐሰቍል ዘንድ አይርከስ።
5 ፤ ራሳቸውን አይላጩ፥ ጢማቸውንም አይላጩ፥ ሥጋቸውንም አይንጩ።
6 ፤ ለአምላካቸው ቅዱሳን ይሁኑ፥ የአምላካቸውንም ስም አያጐስቍሉ፤ የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባንና የአምላካቸውን እንጀራ ያቀርባሉና ቅዱሳን ይሁኑ።
7 ፤ ለአምላኩ የተቀደሰ ነውና ጋለሞታን ሴት ወይም የረከሰችውን አያግባ፤ ወይም ከባልዋ የተፈታችውን አያግባ።
8 ፤ የአምላክህን እንጀራ ያቀርባልና ስለዚህ ትቀድሰዋለህ፤ እኔም የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና እርሱ ቅዱስ ይሁንልህ።
9 ፤ የካህንም ልጅ ራስዋን በግልሙትና ብታረክስ አባትዋን ታረክሰዋለች፤ በእሳት ትቃጠል።
10 ፤ በራሱም ላይ የቅባት ዘይት የፈሰሰበት፥ የክህነትም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ ከወንድሞቹ የበለጠው ካህን ራሱን አይግለጥ ልብሱንም አይቅደድ።
11 ፤ ወደ በድንም ሁሉ አይግባ፥ በአባቱም ወይም በእናቱ አይርከስ።
12 ፤ የአምላኩም ቅባት ዘይት ቅዱስነት በላዩ ነውና ከመቅደስ አይውጣ፥ የአምላኩንም መቅደስ አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
13 ፤ እርሱም ሚስትን በድንግልናዋ ያግባ።
14 ፤ ባልዋ የሞተባትን፥ ወይም የተፋታችውን፥ ወይም ጋለሞታይቱን አያግባ፤ ነገር ግን ከሕዝቡ ድንግሊቱን ያግባ።
15 ፤ እኔም የምቀድሰው እግዚአብሔር ነኝና በሕዝቡ መካከል ዘሩን አያጐስቍል።
16 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
17 ፤ ለአሮን እንዲህ ብለህ ንገረው። ከዘርህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ።
18 ፤ ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም፤ ትርፍ አካል ያለው፥
19 ፤ ወይም እግረ ሰባራ፥ ወይም እጀ ሰባራ፥
20 ፤ ወይም ጐባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዓይነ መጭማጫ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም ጃንደረባ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ።
21 ፤ ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ሰው የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባን ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነው፤ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ።
22 ፤ የቅዱሱንና የቅዱስ ቅዱሳኑን የአምላኩን እንጀራ ይብላ፤
23 ፤ ነገር ግን ነውረኛ ነውና መቅደሶቼን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይግባ፥ ወደ መሠዊያውም አይቅረብ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
24 ፤ ሙሴም ይህን ለአሮን፥ ለልጆቹም፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ነገረ።