ምዕራፍ 15

እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብላችሁ ንገሩአቸው። ማንም ሰው ከሥጋው ፈሳሽ ነገር ቢወጣ፥ ስለሚፈስሰው ነገር ርኩስ ነው።
3 ፤ ስለሚፈስሰው ነገር ርኵስነቱ ይህ ነው፤ ፈሳሹ ነገር ከሥጋው ቢፈስስ ወይም ከመፍሰሱ ቢቆም፥ ርኩስ መሆኑ ነው።
4 ፤ ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚተኛበት መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው፤ የሚቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።
5 ፤ መኝታውንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
6 ፤ ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በተቀመጠበት ነገር ላይ የሚቀመጥበት ሰው ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
7 ፤ ፈሳሽ ነገር ያለበትን የሰውን ሥጋ የሚነካ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
8 ፤ ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በንጹሕ ሰው ላይ ቢተፋ፥ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
9 ፤ ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ሁሉ ርኩስ ነው።
10 ፤ ከበታቹም ያለውን ነገር የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ እነዚህንም ነገሮች የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
11 ፤ ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው እጁን በውኃ ሳይታጠብ የሚነካው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
12 ፤ ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚነካውን የሸክላ ዕቃ ይስበሩት፤ የእንጨቱም ዕቃ ሁሉ በውኃ ይታጠብ።
13 ፤ ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው ከፈሳሹ ነገር ሲነጻ ስለ መንጻቱ ሰባት ቀን ይቈጥራል፤ ልብሱንም ያጥባል፥ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል።
14 ፤ በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዞ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ይመጣል፥ ለካህኑም ይሰጣቸዋል።
15 ፤ ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ፈሳሹ ነገር ያስተሰርይለታል።
16 ፤ የማንም ሰው ዘር ከእርሱ ቢወጣ፥ ገላውን ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
17 ፤ ዘር የነካው ልብስ ሁሉ ቁርበትም ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
18 ፤ ወንዱ በሴቲቱ ቢደርስባት ሁለቱ በውኃ ይታጠባሉ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩሶች ናቸው።
19 ፤ ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት በሥጋዋም ያለው ፈሳሽ ነገር ደም ቢሆን፥ በመርገምዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።
20 ፤ መርገምም ስትሆን የምትተኛበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው፤ የምትቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።
21 ፤ መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
22 ፤ የምትቀመጥበትንም ነገር ሁሉ የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
23 ፤ በመኝታዋም ላይ ወይም በምትቀመጥበት ነገር ላይ ቢሆን ሲነካው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።
24 ፤ ማንም ከእርስዋ ጋር ቢተኛ መርገምዋም ቢነካው፥ ሰባት ቀን ርኩስ ነው፤ የሚተኛበትም መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው።
25 ፤ ሴትም ከመርገም ቀን ሌላ ደምዋ ብዙ ቀን ቢፈስስ፥ ወይም ደምዋ ከመርገምዋ ወራት የሚበልጥ ቢፈስስ፥ በመርገምዋ ወራት እንደ ሆነች እንዲሁ በፈሳሽዋ ርኵስነት ወራት ትሆናለች፤ ርኩስ ናት።
26 ፤ ደምዋም በሚፈስስበት ወራት ሁሉ የምትተኛበት መኝታ ሁሉ በመርገምዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ያለ ይሆንባታል፤ የምትቀመጥበት ነገር ሁሉ እንደ መርገምዋ ርኵስነት ርኵስ ነው።
27 ፤ እነዚህንም ነገሮች የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ልብሱንም ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
28 ፤ ከፈሳሽዋም ብትነጻ ሰባት ቀን ትቈጥራለች ከዚያም በኋላ ንጹሕ ትሆናለች።
29 ፤ በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዛ ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ታመጣቸዋለች።
30 ፤ ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሽዋ ርኵስነት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል።
31 ፤ እንዲሁም በእነርሱ መካከል ያለችውን ማደሪያዬን ባረከሱ ጊዜ፥ በርኵስነታቸው እንዳይሞቱ የእስራኤልን ልጆች ከርኵስነታቸው ለያቸው።
32 ፤ ፈሳሽ ነገር ላለበት ሰው፥ ይረክስም ዘንድ ዘሩ ለሚወጣበት ሰው፥
33 ፤ በመርገምዋም ለታመመች፥ ፈሳሽም ነገር ላለባቸው ለወንድም ለሴትም፥ የረከሰችንም ሴት ለሚገናኝ ሰው ሕጉ ይኸው ነው።