ምዕራፍ 2

ማናቸውም ሰው የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ሲያቀርብ ቍርባኑ ከመልካም ዱቄት ይሁን፤ ዘይትም ያፈስስበታል፥ ዕጣንም ይጨምርበታል፤
2 ፤ ወደ አሮንም ልጆች ወደ ካህናቱ ያመጣዋል፤ ከመልካም ዱቄቱና ከዘይቱም አንድ እፍኝ ሙሉና ዕጣኑን ሁሉ ወስዶ ካህኑ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።
3 ፤ ከእህሉም ቍርባን የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚሆን የእሳት ቍርባን ቅዱስ ቅዱሳን ነው።
4 ፤ በእቶን የተጋገረውን የእህል ቍርባን ስታቀርብ በዘይት የተለወሰ የመልካም ዱቄት የቂጣ እንጐቻ ወይም በዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ይሁን።
5 ፤ ቍርባንህም በምጣድ የተጋገረ የእህል ቍርባን ቢሆን፥ በዘይት የተለወሰ የመልካም ዱቄት ቂጣ ይሁን።
6 ፤ ቈርሰህም ዘይት ታፈስስበታለህ፤ የእህል ቍርባን ነው።
7 ፤ ቍርባንህም በመቀቀያ የበሰለ የእህል ቍርባን ቢሆን፥ ዘይት የገባበት ከመልካም ዱቄት የተደረገ ይሁን።
8 ፤ ከዚህም የተደረገውን የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር ታመጣለህ፤ ለካህኑም ይሰጣል፥ እርሱም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል።
9 ፤ ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መታሰቢያውን አንሥቶ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።
10 ፤ ከእህሉም ቍርባን የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚሆን የእሳት ቍርባን ቅዱስ ቅዱሳን ነው።
11 ፤ እርሾ ያለበት ነገር ማርም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ይሆን ዘንድ አታቀርቡምና ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የእህል ቍርባን ሁሉ እርሾ አይሁንበት።
12 ፤ እነዚህንም የበኵራት ቍርባን አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ እንደ ጣፋጭ ሽታ ግን በመሠዊያው ላይ አይቃጠሉም።
13 ፤ የምታቀርበውን የእህል ቍርባን ሁሉ በጨው ታጣፍጠዋለህ፤ የአምላክህንም ቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቍርባንህ አታጐድልም፤ በቍርባንህ ሁሉ ላይ ጨው ታቀርባለህ።
14 ፤ ከበኵራትም የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ብታቀርብ ስለዚህ ቍርባን በእሳት የተጠበሰና የተፈተገ የእህል እሸት ታቀርባለህ።
15 ፤ ዘይትም ታፈስስበታለህ፥ ዕጣንም ትጨምርበታለህ፤ የእህል ቍርባን ነው።
16 ፤ ካህኑም ከተፈተገው እህል ከዘይቱም ወስዶ ከዕጣኑ ሁሉ ጋር መታሰቢያውን ያቃጥላል፤ ይህ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነው።