ምዕራፍ 3

ቍርባኑም የደኅንነት መሥዋዕት ቢሆን፥ ከላሞች መንጋ ተባት ወይም እንስት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለበትን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ።
2 ፤ እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል።
3 ፤ ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርባል፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥
4 ፤ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል።
5 ፤ የአሮንም ልጆች ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥሉታል፤ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ ነው።
6 ፤ ለእግዚአብሔርም ለደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርበው ቍርባኑ ከበጎች ተባት ወይም እንስት ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ያቀርባል።
7 ፤ ለቍርባኑ ጠቦትን ቢያቀርብ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤
8 ፤ እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛው ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል።
9 ፤ ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርባል፤ ስቡን፥ እስከ ጀርባውም ድረስ የተቈረጠ ላቱን ሁሉ፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥
10 ፤ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል።
11 ፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ በእሳት ላይ ለእግዚአብሔር የተደረገ የቍርባን መብል ነው።
12 ፤ ቍርባኑም ፍየል ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤
13 ፤ እጁንም በራሱ ላይ ይጭንበታል፥ በመገናኛውም ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል።
14 ፤ ከእርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርበዋል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥
15 ፤ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል።
16 ፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ በእሳት ላይ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የተደረገ መብል ነው። ስቡ ሁሉ ለእግዚአብሔር ነው።
17 ፤ ስብና ደም እንዳትበሉ በምትኖሩበት ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው።